Tuesday, November 11, 2014

መሞት አያስፈራም!

ዲቮሽን ቁ.62/07     ማክሰኞ፣ ሕዳር 2/07 ዓ.ም.
(በመጋቢ ተስፋሁን ሐጢያ)


መሞት አያስፈራም!

መልካሙን ገድል ተጋድዬአለሁ፥ ሩጫውን ጨርሼአለሁ፥ ሃይማኖትን ጠብቄአለሁ፤ ወደ ፊት የጽድቅ አክሊል ተዘጋጅቶልኛል (2 ጢሞ 4፡7-8)

ሐዋርያው ጳውሎስ ይህን መልዕክት ለወጣቱ ጢሞቴዎስ ሲጽፍ ከአፍንጫው ሥር የሞት ሽታ እየሸተተው ነበር፡፡ ሞትን የሚያህል ታላቅና አስፈሪ ነገር ተደግሶበት ሳለ ያለ ምንም ፍርሃት ሞትን ለማጋፈጥ መዘጋጀቱን ይገልጻል፡፡ ሐዋርያው ሞትን ያልፈራው በአራት ዋና ዋና ምክንያቶች ነው፡፡ (1ኛ) መልካሙን ገድል በመጋደሉ፣ (2ኛ) ሩጫውን በመፈጸሙ፣ (3ኛ) በእምነት ጸንቶ በመቆሙ፣ (4ኛ) የጽድቅ አክሊል ስለተዘጋጀለት ነው፡፡

ታውቃላችሁ፣ በኑሮአችን መልካሙን የእምነት ገድል እየተጋደልን ከሆነ፣ የእንት ሩጫችንን ፈጽመን እንደሆነ እና በእምነታችን ጸንተን ቆመን እንደሆነ መሞት አያስፈራም! ምድራዊ ኑሮአቸውን በእምነት የሚኖሩ፣ የሕይወት ሩጫቸውን በመልካም የሚሮጡ ሞትን አይፈሩትም!

ወዳጆች ሆይ፣ እውነተኛ አማኞችን ሞት አያስፈራም! የተፈጠርንለትን አውቀነው ከሆነ፣ የተጠራንለትን ኖረነው ከሆነ፣ የቤት ሥራችንን ፈጽመን ከሆነ መሞት አያስፈራም! ታላቁን ተልዕኮ ፈጽመን ከሆነ፣ ደቀመዛሙርትን አፍርተን ከሆነ መሞት አያስፈራም! ዕውቀት ሀብታችንን፣ ጉልበት ጊዜያችንን ለወንጌሉ ሥራ አውለን ከሆነ መሞት አያስፈራም!

ወዳጆች ሆይ፣ በተገለጠ እውነት መኖር እስከቻልን፣ በተሰጠን ጸጋ እስካገለገልን፣ በተቀበልነው ሸክም መሮጥ እስከቻልን፣ መሞት አያስፈራም! ለተመለከትነው ራዕይ መታዘዝ ከቻልን፣ ፈተናን በትጋት፣ ኑሮን በእምነት፣ ሩጫን በትዕግስት መሮጥ እስከቻልን መሞት አያስፈራም!
ወገኖች ሆይ፣ ለእውነት እየታዘዝን የእውነት ብንኖር መሞት አያስፈራም! ፍቅር፥ ደስታ፥ ሰላም፥ ትዕግሥት፥ ቸርነትን መላበስ ከቻልን መሞት አያስፈራም!  እምነት፥ ራስን መግዛት፣ በጎነት፥ የውሃት ከተጎናጸፍን መሞት አያስፈራም!  

ወገኖች ሆይ፣ የእውነት ቀበቶ ታጥቀን፣ የጽድቅ ጥሩር ለብሰን፣ የሰላምን ወንጌል በእግራችን ተጫምተን ከተዘጋጀን መሞት አያስፈራም!  የሚንንቀለቀለውን የሰይጣንን ፍላጻ የምንመክትበትን የእምነትን ጋሻ አንግበን ከሆነ መሞት አያስፈራም!  የድኅነትን ራስ ቁር በራሳችን ላይ ደፍተን፣ የእግዚአብሔርን ቃል እንደ መንፈስ ሰይፍ ጨብጠን ከሆነ መሞት አያስፈራም!

-------------------------

(እባክዎ፣ ይህን ዕለታዊ ዲቮሽን ላይክ ያድርጉ፣ ወዳጅ ጓደኞችዎም እንዲያገኙ ያግዙ፡፡ ጌታ ይባርክዎ!)

No comments:

Post a Comment