Wednesday, November 12, 2014

ሞተን ተሰውረናል!

ዲቮሽን ቁ.63/07     ረቡዕ፣ ሕዳር 3/07 ዓ.ም.
(በመጋቢ ተስፋሁን ሐጢያ)

ሞተን ተሰውረናል!

ሞታችኋልና፥ ሕይወታችሁም በእግዚአብሔር ከክርስቶስ ጋር ተሰውሮአልና (ቆላ 3፡3)

ዳግመኛ የተወለዱ (እውነተኛ) ክርስቲያኖች ለኃጢአት፣ ለሥጋ፣ ለዓለም የሞቱ ናቸው! ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ የተጠመቅን ሁላችን ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ ስለተጠመቅን already ሞተናል! የሕይወት ቁርኝታችን ከክርስቶስ ጋራ ጥብቅ ስለሆነ የፍጻሜያችን ነገር አያስጨንቀንም! የሞትን ስለሆነ ሊያስፈራን የሚችል ሌላ ሞትም የለም! የሞተ ሰው ደግሞ ሞትን አይፈራውም!

ወገኖች ሆይ፣ እውነተኛ አማኞች already የሞቱ ብቻ አይደሉም– ሕይወታቸው ከክርስቶስ ጋር የተጣበቀ ከመሆኑ የተነሣ ከራዳር ውጭ የተሰወሩ ናቸው! እውነተኛ አማኞች ከሞት ጥቃት ዒላማ በአስተማማኝ ሁኔታ የተጠበቁ፣ የተደበቁ ናቸው! እውነተኛ አማኞችን ዓለም ራሷ እንኳ ፈጽሞ አታውቃቸውም!

ወገኖች ሆይ፣ የእውነተኛ አማኞች መንፈሳዊ ሕይወት ከዓለም ግንዛቤ የተሰወረ ነው፡፡ አማኞች ያልሆኑ የሕይወት ዘይቤያችንን፣ አስተሳሰባችንን ፈጽሞ አያውቁም!  አማኞች ያልሆኑ አመለካከታችንን፣ አካሄዳችንን፣ ቋንቋ ፈሊጣችንን መረዳት አይችሉም! ከእምነታችን ገብተው፣ ከመንፈሳችን ጠልቀው፣ ከሕይወታችን ዘልቀው መመርመር አይችሉም!

ወገኖች ሆይ፣ በውስጣችን ያለው ዓለም የማያየው፣ ዓለም የማያውቀው፣ ሊቀበል የማይችለው የእውነት መንፈስ ነው! የሰማዩ አባት ምን ያህል እንደወደደን፣ ‹‹የእግዚአብሔር ልጆች›› ተብለን ልንጠራ እንዴት እንደበቃን ዓለም አይረዳም! የእግዚአብሔርን ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስን ያላወቀ ዓለም እኛን አያውቀንም!

ወገኖች ሆይ፣ ከክርስቶስ ጋር ሞተን፣ ከክርስቶስ ጋር ተሰውረናል! የሞተ ሰው ደግሞ ከዚህ ዓለም ነገር እንደሚለይ ሁሉ እውነተኛ ሕይወታችን ከዓለም ተለይቶ ከክርስቶስ ጋር በሰማይ ይገኛል! በሰማይ ከክርስቶስ ጋር የተሰወርን ስለሆነ በምድር ላይ ስንኖር ሕይወታችንን ከምድራዊ ነገር፣ ከዓለም እርኩሰት ልንጠብቅ ይገባል!

ወገኖች ሆይ፣ በገዛ ምርጫችን ከከፍታው ወርደን፣ ከጥበቃው ወጥተን፣ ለጠላት ዒላማ ተጋላጭ እንዳንሆን ጥንቃቄ እናድርግ! በሰይጣን ሽንገላ በዓለም በመታለል ከምሕረቱ ቀጣና፣ ከድነቱ ዋስትና እንዳንወጣ፣ በሞት ወጥመድ ሥር ተጠልፈን እንዳንወድቅ፣ ወድቀን እንዳንጠፋ ጌታ ይጠብቀን!

-------------------------

(እባክዎ፣ ይህን ዕለታዊ ዲቮሽን ላይክ ያድርጉ፣ ወዳጅ ጓደኞችዎም እንዲያገኙ ያግዙ፡፡ ጌታ ይባርክዎ!)

No comments:

Post a Comment