ዲቮሽን ቁ.60/07 እሁድ፣ ጥቅምት
30/07 ዓ.ም.
(በመጋቢ ተስፋሁን ሐጢያ)
ችግርዎ ቢባባስ!
የምናመልከው
አምላካችን ከሚነድደው ከእሳቱ እቶን ያድነን ዘንድ ይችላል ከእጅህም ያድነናል፥ ንጉሥ ሆይ! ነገር ግን፥ ንጉሥ ሆይ፥ እርሱ ባያድነን፥ አማልክትህን እንዳናመልክ ላቆምኸውም ለወርቁ ምስል እንዳንሰግድለት እወቅ አሉት። የዚያን ጊዜም ናቡከደነፆር … የእቶንም እሳት ይነድድ ከነበረው ይልቅ ሰባት እጥፍ አድርገው እንዲያነድዱት አዘዘ። 3፡17 -19
ሲድራቅ
ሚሳቅና አብደናጎ ለናቡከደነጾር
ጣዖት ባለመስገዳቸው ተከስሰው ለፍርድ ወደ ንጉሡ ቀርበዋል፡፡ በወንጀለኛ መቅጫ ሕጉ መሠረት በእቶን እሳት ላይ እንዳይጣሉ ንጉሡ
ቢያባብላቸው በአቋማቸው ጸኑ፡፡ በዚህ የተቆጣው ንጉሥ የእቶኑ እሳት ወደ ሰባት እጥፍ አድጎ እንዲነድድና እንዲጣሉ አዘዘ፡፡
ወዳጄ ሆይ፣ ችግርዎ ቢባባስ ምን ያደርጋሉ? እንደሲድራቅ እንደ ሚሳቅና እንደ አብደናጎ ጌታን ይታመኑ! ጌታን መተማመን ለእግዚአብሔር
ችሎታ እውቅና መስጠት ነው! ለሥልጣኑ ብርታት፣ ለኃይሉ ታላቅነት፣ እራስን መስጠት ነው! ጌታን መተማመን በሁሉ ቻይነቱ ላይ
እምነት ማሳደር ነው!
ወዳጄ ሆይ፣ ሲድራቅ
ሚሳቅና አብደናጎ ችግር
ሲባባስባቸው የወሰዱት የመጀመሪያ እርምጃ ጌታን መታመን ነው! ጌታን ስንታመን የውስጥ ሰውነታችን ጥንካሬ ያገኛል፡፡ የውስጥ
ሰውነታችን ጥንካሬ ሲያገኝ መጽናት ይሆንልናል! ከዚህ ጽናት የተነሳም ነው ባያድናቸውም እንኳ ለጣዖት ላለመስገድ ቆራጥ ውሳኔ
ያደረጉት!
ታውቃላችሁ፣ ጌታን ለመታመን እርሱን ማወቅ ያሻል! ያላወቁትን ጌታ መታመን
ይከብዳል! ታውቃላችሁ፣ ወጣቶቹ ጌታን ያውቁት ነበር! ያ ባይሆን ኖሮ በንጉሥ ፊት ለመቆም አቅም አያገኙም! ከእሰጥ–አገባው ፈጽመው
አይገቡም! ነፍሳቸውን አስይዘው አይከራከሩም!
ወዳጄ ሆይ፣ በክርስቶስ ኢየሱስ እግዚአብሔርን እየመሰሉ የሚኖሩ ሁሉ ልዩ ልዩ ፈተናዎች
ይጋፈጣሉ! ጻድቃን ከመከራና ችግር ጋር ጉሮሮ ለጉሮሮ እየተናነቁ የመታገሉን ሚስጥር ይለማመዳሉ! አንዳንዴም በትግሉ ሜዳ ላይ
መቁሰል ያጋጥማል!
ወዳጄ ሆይ፣ መቁሰልዎ ሳያንስ፣ ቁስልዎ ቢያብጥብዎ–ያበጠው መርቅዞ–ቢጠዘጥዝዎ–የጥዝጣዜው
ብዛት እንቅልፍ ቢነሳዎ ከነሲድራቅ ይማሩ! ሕመምዎ ቢባባስ፣ ችግር ቢወሳሰብ፣ ጌታን ይታመኑ! ለጣዖት አይስገዱ! ለጠላት ፊት
አይስጡ! መግደልም ማዳንም የሚችለውን ጌታ እርሱን ይታመኑ!
-------------------------
(ይህን
ዕለታዊ
ዲቮሽን
ላይክና ሼር ያድርጉ፣ ወዳጅ ጓደኞችዎም
እንዲያገኙ
ያግዙ፡፡ ጌታ ይባርክዎ!)
No comments:
Post a Comment