Saturday, November 8, 2014

የሚረዳዎት ባይኖር!

ዲቮሽን ቁ.59/07     ቅዳሜ፣ ጥቅምት 29/07 ዓ.ም.
(በመጋቢ ተስፋሁን ሐጢያ)

የሚረዳዎ ባይኖር!

ከማኅፀን ጀምሮ በአንተ ላይ ተጣልሁ ከእናቴ ሆድ ጀምረህ አንተ አምላኬ ነህ። ጭንቀት ቀርባለችና የሚረዳኝም የለምና ከእኔ አትራቅ(መዝ 22፡10-11)።

አንዳንዴ በሕይወታችን ከባድ ፈተናዎች ያልፋሉ! እነዚህ ፈተናዎች ከሚያደርሱብን ጉዳት የተነሳ ቆሞ ለመራመድ፣ እህል ውሃ መውሰድ፣ መኝታና እረፍት ማድረግ እስከማንችል ድረስ አቅም እናጣለን! በእንዲህ ዓይነት ወቅት፣ የልብ የአንጀታችን ጠልቆ የሚገባው፣ የውስጥ ስሜታችን ዘልቆ የሚታየው ወዳጅ ያስፈልገናል!

እንደየልባችን፣ እንደስሜታችን፣ እንደጉዳታችን የሚንከባከበን ረዳት እንፈልጋለን! እንደቁስለታችን፣ እንደስብራታችን አክሞ የሚያድን ወዳጅ እንሻለን! እንደየሐዘናችን የሚያስተዛዝነን፣ እንደሕመማችን ታምሞ የሚያክመን የልብ ሰው እንፈልጋለን!

ታውቃላችሁ፣ ከሰው ልጆች መካከል እንዲህ ያለ ረዳት፣ እንዲህ ያለ ወዳጅ የለም! የጉዳታችን ልኬት፣ የሐዘናችን ጥልቀት ለሰዎች አይታይም! አባትና እናት፣ ወንድምና እህት፣ ዘመድ አዝማዳችን የውስጥን አይረዱም! ባልና ሚስታችን፣ እጮኛ ሚዜአችን፣ ወዳጅ ጓደኛችን የልብን አያውቁም!  

ወዳጄ ሆይ፣  ከሰው ልጆች መሃል የልብ የኩላሊት፣ የውስጥ የአንጀት የሚረዳ ባይኖር፣ ጌታ አለልዎ! በፈተና ጊዜ፣ በጭንቀት መካከል ከአጠገብ የማይርቅ እግዚአብሔር አለዎ! በወሳኝ ደቂቃ፣ በምጥ በጣር ጊዜ፣ ፈጥኖ ደራሽ ጌታ በዙፋኑ ላይ አለ!

ወዳጄ ሆይ፣ በእናታችን ማኅፀን ሥጋ ነፍሳችንን፣ ልብ ኩላሊታችን የሠራው ጌታ የውስጥ የውጫችንን ያውቃል! ሐዘን ደስታችንን፣ ጉዳት ስብራታችንን፣ ሁሉን ነገራችንን ያውቃል! የፈጠረን ጌታ፣ የሠራን እግዚአብሔር፣ በጥልቀት ያውቀናል!

ወዳጄ ሆይ፣ የሚረዳዎ ባይኖር እግዚአብሔር አለልዎት! የሐዘንዎን ጥልቀት የሚያውቅ፣ የጉዳትዎን ብርታት የሚመለከት እግዚአብሔር  ድካምዎን የሚያግዝ፣ እንባዎን የሚያብስ፣ ከአጠገብዎ የማይርቅ ጌታ አለልዎት!

-------------------------

(ይህን ዕለታዊ ዲቮሽን ላይክና ሼር ያድርጉ፣ ወዳጅ ጓደኞችዎም እንዲያገኙ ያግዙ፡፡ ጌታ ይባርክዎ!)

No comments:

Post a Comment