ዲቮሽን ቁ.58/07 አርብ፣ ጥቅምት
28/07 ዓ.ም.
(በመጋቢ ተስፋሁን ሐጢያ)
ዲያስፖራ (#3) – ድንኳን ሰፊዎች!
…
ጳውሎስ ከአቴና ወደ ቆሮንቶስ ሄደ፡፡ በቆሮንቶስም በጳንጦስ ተወልዶ ያደገ አቂላ የሚባል አንድ አይሁዳዊ አገኘ፡፡ አቂላ ከሚስቱ ከጵርስቅላ ጋር ከኢጣልያ
ወደ ቆሮንቶስ ገና መምጣቱ ነበር፡፡ …ጳውሎስም እንደ አቂላና ጵርስቅላ ድንኳን መስፋት ይችል ስለነበር፣ ማረፊያውን ከእነርሱ
ዘንድ አደረገ፡፡ በየሰንበቱም ወደ ምኵራብ እየሄደ፣ ለአይሁድና የግሪክ ሰዎች ስለክርስቶስ ያስተምር፣ ያስረዳም ነበር።
ክርስቲያኖች
በተለያዩ ምክንያቶች ከትውልድ አገራቸው ሊሰደዱ ይችላሉ፡፡ ከአቂላና ጵርስቅላ የምናየውም ይህን ነው፡፡ ባልና ሚስቱ ሮማዊ
ዜግነት ያላቸው አይሁዳዊያን ክርስቲያኖች ናቸው፡፡ የሮማው ንጉሠ ነገሥት ቀላውዴዎስ አይሁድ ሮምን ለቅቀው እንዲወጡ ትዕዛዝ ሲያወጣ
ባልና ሚስቱ ከትውልድ አገራቸው ተሰደዱ፡፡
ታውቃላችሁ፣
ከሞቀ ቤታቸው ባዶ እጃቸውን የተሰደዱት ባልና ሚስቱ፣ በእጃቸው ላይ የስፌት ሙያ ጥበብ ነበራቸው፡፡ ድንኳን፣ ቆዳና ሌጦ፣
እንዲሁም ማናቸውም አልባሳት እየሰፉ በስደት አገር ደህና ኑሮ ይኖራሉ፡፡ ባልና ሚስቱ ከራሳቸውም አልፈው እነደእነርሱ በወንጌልን
ሥራ ለተሰማሩ እንደ ሐዋርያ ጳውሎስና ለሌሎችም መጠጊያ መሆን ችለዋል፡፡
ወገኖች
ሆይ፣ ባልና ሚስቱ በነበራቸው የእጅ ጥበብ ሙያ የተነሳ በአቴና እጅግ የተከበሩ ነበሩ፡፡ ወደ ቆሮንቶስ ሲመጡም በእጅ ሙያቸው ምክንያት
ቀድሞ የነበራቸው ክብር አልተለያቸውም፡፡ ሐዋርያ ጳውሎስን የመሰለ ታላቅ የወንጌል አገልጋይ በቤታቸው ተቀብለው ሊያኖሩት በቅተዋል፡፡
ወደ ኤፌሶን ሲመጡም በነበራቸው የእጅ ሙያ ምክንያት በሰው ዘንድ ከፍተኛ እውቅና ነበራቸው፡፡ ከዚህም የተነሳ አፖሎን የመሳሰሉ
ታላላቅ ሰዎችን እንኳ ከእግራቸው ሥር አስቀምጠው ስለክርስቶስ ለማስተማርና ደቀመዝሙር ለማድረግም በቅተዋል፡፡
ወገኖች
ሆይ፣ አቂላና ጵርስቅላ እንማር! የልብስ ስፌት፣ የምግብ ዝግጅት፣ የካፌና ሬስቶራንት፣ የእርሻና የእንስሳት ወይንም ማናቸውም
ዓይነት ሙያ ይኑረን! ግንበኛ አናጺነት፣ ቀለም ቀብነት፣ ዲዛይን ዴኮሬሽን ወይንም ማናቸውም ዓይነት ሙያ ይኑረን! የቀለም፣
የቋንቋ፣ የሳይንስ የቴክኖሎጂ፣ የሙዚቃ፣ የስነሥዕል፣ የአርት የትወና ወይንም የስፖርት፣ የአትሌቲክስ፣ የማርሻል አርት፣ የዋና፣
ወይንም ማናቸውም ዓይነት ሙያ ይኑረን!
ወገኖች
ሆይ፣ የአንድ ሙያ ባለቤት ከሆንን በየሄድንበት አገር አንገት ሳንደፋ መኖር እንችላለን፡፡ ከራሳችን አልፈን ለሌላ እንተርፋለን!
ለወንጌል አገልግሎት ዕድል እንከፍታለን! የወንጌል አገልጋዮችን እንደግፍበታለን! (ተፈጸመ)
-------------------------
(ይህን
ዕለታዊ
ዲቮሽን
ላይክና ሼር ያድርጉ፣ ወዳጅ ጓደኞችዎም
እንዲያገኙ
ያግዙ፡፡ ጌታ ይባርክዎ!)
No comments:
Post a Comment