Monday, December 1, 2014

የጴንጠቆስጤነት አቡጊዳ(#2) – በልሣን መናገር!

ዲቮሽን ቁ.82/07     ሰኞ፣ ሕዳር 22/07 ዓ.ም.
(በመጋቢ ተስፋሁን ሐጢያ)

የጴንጠቆስጤነት አቡጊዳ(#2) – በልሣን መናገር!

…እንደ እሳትም የተከፋፈሉ ልሳኖች ታዩአቸው፤ በያንዳንዳቸውም ላይ ተቀመጡባቸው። በሁሉም መንፈስ ቅዱስ ሞላባቸው፥ መንፈስም ይናገሩ ዘንድ እንደ ሰጣቸው በሌላ ልሳኖች ይናገሩ ጀመር (የሐዋ 2፡3-4)፡፡
(የሐዋ 2፡1-2)፡፡

ወገኖች ሆይ፣ እስራኤላዊያን በምድረ በዳ ሲሄዱ እግዚአብሔር አብሮአቸው መኖሩን እንዲያውቁ በግልጽ የሚታይ ምልክት ሰጥቷቸው ነበር– ቀን ቀን የደመና አምድ፣ ማታ ማታ የእሳት አምድ፡፡ በጴንጠቆስጤ ዕለትም ይኼው ክስተት ተደግሟል፡፡ ደቀመዛሙርቱ በመንፈስ ቅዱስ ሲጠመቁ ዓውሎ ነፋስ (የደመና አምድ) እና እሳትም ልሳኖች (የእሳት አምድ) ታይቷቸዋል፡፡

ታያላችሁ፣ እግዚአብሔር በብሉይም ሆነ በአዲስ ኪዳን ሕዝቡን እየመራ ስለመሆኑ ሕዝቡ እንዲያውቅ ግልጽ ምልክቶች ያስፈልጋሉ ማለት ነው፡፡

ታውቃላችሁ፣ በልሳን መናገር (በግሪክ ቋንቋ፣ ግሎሳላሊያ) በመንፈስ ቅዱስ ለመጠመቃችን ምልክት ነው! የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት ስለመቀበል አለመቀበላችን ምልክቱ ደረቅ የቃላት ክርክር ሳይሆን ግልጽ የሆነ በአዲስ ቋንቋ መናገር ነው፡፡

ወገኖች ሆይ፣ በሙሴ ዘመን የነበሩትን ኤልዳድና ሞዳድ አስቡ(ዘሁ 11)፡፡ እነዚህ ሁለቱ ሰዎች ሙሴን በአመራር እንዲደግፉ ከተመረጡ ሰባ ሰዎች ስም ዝርዝር ውስጥ ነበሩ፡፡ ሰባዎቹ ሰዎች በድንገት ተጠርተው እግዚአብሔር በሙሴ ላይ ካለው መንፈስ ወስዶ  ሲያፈስባቸው፣ ሁሉም ትንቢት ተናገሩ፡፡ ይህም ሁሉም መሪ መንፈሱን ለመቀበሉ ምልክት ነበር፡፡

ወገኖች ሆይ፣ አስቸኳይ ስብሰባው ሲጠራ ኤልዳድና ሞዳድ በሰፈሩ አልነበሩም፡፡ ሆኖም፣ የእግዚአብሔር መንፈስ ያሉበት ቦታ ድረስ በመሄድ ከሌሎቹ መሪዎች እኩል መንፈሱን ተቀብለው ትንቢት ይናገሩ ነበር፡፡ ይህ ምልክት እነርሱም መንፈሱን ለመቀበላቸው ማስረጃ ነበር፡፡

ወገኖች ሆይ፣ በልሳን መናገር ተአምራት ነው፡፡ ያልማሩትን ቋንቋ ሳይኮላተፉና ሳንተፋተፉ መናገር መቻል ተአምራት ነው፡፡ ባልተማሩት ቋንቋ፣ በማያውቁት ቋንቋ፣ በማይረዱት ቋንቋ ልብን የሚነካ ጥርት ያለ መልዕክት ለአድማጭ ማስተላለፍ መቻል ተአምራት ነው፡፡ ይህ ተአምራት በመንፈስ ቅዱስ ለመጠመቃችን መነሻ ምልክት፣ ግልጽ ማስረጃ ነው!

ታውቃላችሁ፣ በልሳን መናገር ሁለት ጥቅም አለው–አንዱ ራስን ለማነጽ ሁለተኛው ጉባኤውን ለማነጽ፡፡

ወገኖች ሆይ፣ ‹‹ራስን ማነጽ›› ማለት ምን ማለት ነው? እንዴት መጸለይ እንደሚገባን አናውቅምና፥ በልሳን ስንጸልይ መንፈስ ቅዱስ ራሱ በማይነገር መቃተት ይማልድልናል፡፡ ሰዎች ስለሆንን ድካም አለብንና፣ በልሳን ስንጸልይ መንፈስ ድካማችንን ያግዛል(ሮሜ 8፡26)፡፡ በዚህም ራሳችን ይታነጻል፡፡

ወገኖች ሆይ፣ ሰዎች ስለሆንን የእግዚአብሔርን ሐሳብ ጠንቅቀን አናውቅምና፣ በልሳን ስንጸልይ፣ የሰውን ልብ የሚመረምረውና የእግዚአብሔርም ሐሳብ ምን እንደ ሆነ የሚያውቀው መንፈስ ቅዱስ እንደ ፈቃዱ እንድንጸልይ ይረዳናል(ሮሜ 8፡27)። በዚህም ራሳችን ይታነጻል፡፡

ወገኖች ሆይ፣ በልሳን ስንጸልይ ጉባኤ የሚታነጸው ደግሞ ልሳናችን ተተርጉሞ ለሕዝብ ሲቀርብ ነው፡፡ በበዓለ ሀምሳው ዕለት ከዓለም አካባቢ የመጡ ዲያስፖራዎች በልሳኖች አማካይነት መዕልክት ደርሷቸዋል፡፡ በዚህም ታንጸው ጌታን ተቀብለዋል፡፡ ታያላችሁ፣ በጉባኤ ውስጥ ሰዎች በልሳን እንዳይናገሩ የምንከለክለው ያልተገባ ድርጊት ነው፡፡ የበዓለ ሀምሳው ልምምድ የሚነገረን ሁሉም በልሳን ይናገሩ እንደነበር ነው፡፡

ታውቃላችሁ፣ በጉባኤ ውስጥ በልሳኖች መናገር ከፍተኛ ጥቅም አለው! በልሳኖች መናገር ለማያምኑ ምልክት ነው (1 ቆሮ 14፡22)፡፡ በመንፈስ ቅዱስ የተጠመቁ ሁሉ በልሳን ይናገራሉ፡፡ በጉባኤ ውስጥ ሁሉም በልሳን ቢናገር ራሱን ማነጽ ይችላል፡፡ ነገር ግን በጉባኤ ውስጥ ስንሆን የጋራ የሆነ የአካል መተናነጽ እንዲኖር በልሳን መናገር ተራ በተራ ቢሆን የተመረጠ ነው(1 ቆሮ 12፡30፣ 14፡27፣31)፡፡

ወገኖች ሆይ፣ በጉባኤ ውስጥ ሁሉም አንድ ላይ ልሳን ቢናገሩ ጉባኤው ይታነጻልን? ሁሉም አንድ ላይ ቢናገሩ ራሳቸውን ብቻ እንጂ ጉባኤውን አያንጹምና፣ ተራ በተራ መናገሩ ይሻላል ማለት ነው! ተራ በተራ መናገሩ የበለጠ መደማመጥ እንዲኖር ዕድል ይሰጣልና ተራ በተራ መናገሩ ይሻላል ማለት ነው!

ሊረሳ የማይገባው ነጥብ–ጴንጠቆስጤነት ለ ልሳን መናገር ሊተረጎም አይችልም፡፡ በበዓለ ሀምሳው ዕለት እያንዳንዱ ሰው በልሳን ይናገር ነበር፡፡ ከተደመጠው የልሳን መናገር ጩኸትና ድምጽ የተነሳ ወደ ሶስት ሺህ የሚደርሱ ሰዎች ለማየት መምጣታቸው አይካድም!

ሊረሳ የማይገባው ነጥብ–ጴንጠቆስጤነት ካለ የልሳን ጩኸት መከልከል አይቻልም! በበዓለ ሀምሳው ዕለት ከዓለም ሁሉ አቅጣጫ የመጩት ሶስት ሺህ ሰዎች በሰሙት የጉባኤ የልሳን ጩኸት በገዛ ቋንቋቸው መልዕክት እንደሰሙ፣ እንደተደነቁና እንደተገረሙ፣ ልባቸው እንደተነካና እንደተለወጡ እንደተጠመቁም መካድ አይቻልም!

ሊረሳ የማይገባው ነጥብ–ሁሉ በስርዓት ይሁን እንጂ፣ ሕዝባችን በጉባኤ መካከል በልሳን እንዳይጸይ መገደብ አይገባም! በጉባኤ መካከል በልሳን መጸለይ ይጠቅም እንደሁ እንጂ፣ ጉዳት አያመጣም፡፡

--------------------------------

(ትምህርቱ ጠቅምዎታል? እንግዲያውስ ላይክና ሼር ያድርጉ፣ ወዳጅ ጓደኞችም እንዲያገኙ ያግዙ፡፡ ጌታ ይባርክዎ!)

No comments:

Post a Comment