Friday, November 14, 2014

ከስግብግብነት ይጠንቀቁ!

ዲቮሽን ቁ.65/07     አርብ፣ ሕዳር 5/07 ዓ.ም.
(በመጋቢ ተስፋሁን ሐጢያ)

ከስግብግብነት ይጠንቀቁ!

የሰው ሕይወቱ በሀብቱ ብዛት የተመሠረተ ስላልሆነ፣ ተጠንቀቁ፤ ከስግብግብነትም ሁሉ ራሳችሁንም ጠብቁ››(ሉቃ 12፡15)

በዚህ ምድር ላይ ስንኖር ኑሮ ከባድ ፈተና እንደሆነ ግልጽ ነው! ይህንን ፈተና ለመቋቋም፣ ለማሸነፍና ለመቀልበስ የሰው ልጅ ቀን ማታ ይተጋል! የሰው ልጅ ጥሮ ግሮ ምግቡን ያገኛል! የሚፈልገውን ለማግኘት የማይፈልውን ያደርጋል! ሀብት ለመሰብሰብ ወዙንና ላቡን ያንጠፈጥፋል! ሲሰሩ መክበሩ፣ ከብሮም መበልጸጉ ከጌታ የተሰጠ ትዕዛዝ ነውና የተፈቀደ ነው! ነገር ግን ለሀብት እንዳንስገበገብ መጠንቀቅ ይገባል!

ብዙ ሰዎች ገንዘብ ማግኘት ሲጀምሩ ይስገበገባሉ! ያገኟትን ቋጥረው፣ የቋጠሯትን ቀብረው በስስት ይይዛሉ! በቋጠሩ መጠን፣ ብዙ እንደሚያጠራቅሙ፣ ባጠራቀሙም መጠን ብዙ የሚደሰቱ አድርገው ያስባሉ! አስራትና መባ ስጦታቸውን ሳይቀር መሰስት ይይዛሉ! በዚህም ሀብታቸውን ለተምች ለኩብኩባ፣ ለብልና ዝገት፣ ለነቀዝ ለጥፋት ያጋልጣሉ!

ወዳጄ ሆይ፣ የሰው ሕይወቱ በሀብቱ ብዛት ላይ የተመሠረተ አይደለምና በሀብት ከመደገፍ ይጠንቀቁ! እረፍት የሚገኘው ብዙ ባከማቹ፣ ባተረፉ አይደለምና ይህንን ይወቁ! መንፈሳዊ ሰው የሚያገኘው ሀብቱ የሚይዘው ጥሪቱ የጌታ ነው!

ወዳጄ ሆይ፣ መንፈሳዊ ሰው ለጋስና ቸር ነው! ለመንፈሳዊ ሰው የብልጥግናው ቀመር፣ ብዙ ለመቀበል ብዙ በመስጠት ነው! መንፈሳዊ ሰው በመከራ ውስጥም ቢሆን፣ በፈተናም ቢሆን፣ በድህነትም ቢሆን ሕይወቱ ለጋስ ነው!

ወዳጄ ሆይ፣ መንፈሳዊ ሰው ከሙላቱም ከጉድለቱም መለገስ ይወዳል! መንፈሳዊ ሰው አቅሙ በፈቀደ፣ ከአቅሙም በበለጠ ልግስና ያበዛል! የልግስናውም ብዛት በረከቱን እንዲያበዛ ጠንቅቆ ይረዳል!

ወዳጄ ሆይ፣ ብልጥግና ጤዛ፣ ሀብትም ጭጋግ ነውና ለሀብት አይስገብገቡ! ላብዎን አንጠፍጥፈው፣ ንዋይዎን አፍስሰው ያመጡት ቢሆንም ለሀብት አይስገብገቡ! የሚያገኙትን ሀብት፣ ብዙ በሚወልደው፣ ትርፉ በሚባዛው በጌታ ባንክ ውስጥ ዲፖዚት ያድርጉ!

-------------------------

(እባክዎ፣ ይህን ዕለታዊ ዲቮሽን ላይክ ያድርጉ፣ ወዳጅ ጓደኞችዎም እንዲያገኙ ያግዙ፡፡ ጌታ ይባርክዎ!)

No comments:

Post a Comment