Thursday, November 13, 2014

ከአሕዛብ አትማር!

ዲቮሽን ቁ.64/07     ሐሙስ፣ ሕዳር 4/07 ዓ.ም.
(በመጋቢ ተስፋሁን ሐጢያ)

ከአሕዛብ አትማር!

አምላክህ እግዚአብሔር ወደሚሰጥህ ምድር በገባህ ጊዜ እነዚያ አሕዛብ የሚያደርጉትን ርኵሰት ታደርግ ዘንድ አትማር። (ዘዳ 18፡9)

ምድርና ሞላዋ የእግዚአብሔር ናትና፣ የእግዚአብሔር ሰው ከአንዱ የምድር አካባቢ ወደ ሌላው የምድር አካባቢ ሊሄድ ይችላል፡፡ ከሚኖሩበት ሀገር ሕዝብ ጋር አብሮ ለመኖር፣ ቋንቋና ባህሉን፣ ሥራና ምግባሩን መማር ይገባል፡፡ ነገር ግን ለእግዚአብሔር ሰው የሀገሩን እርኩሰት መማር የተከለከለ ነው!

የዛሬው ዘመን የአሕዛብ ሥልጣኔ ሰይጥኗል! ዲያብሎስ የሰውን ሥልጣኔ ከእጁ አስገብቷል! ኢንተርኔቱን፣ ኢንተርቴይመንቱን፣ ሙዚቃና ዳንሱን፣ ባህል ሐይማኖቱን፣ ፋሽን ኢንዳስትሪውን መቆጣጠር ችሏል!

ወገኖች ሆይ፣ ዲያብሎስ በስመ ሥልጣኔ ስነ ሥይጣኔን በሰው ልጆች ላይ ጭኗል! የዘመኑን ሰው ልብሱን እየገፈፈ ራቁት ማስኬድ ችሏል! የወንዱን ጾታ ሴት፣ የሴቱን ወንድ አድርጓል! የጎዳና ዝሙት፣ ግብረሰዶማዊነት፣ መዳራት እርኩሰት የተለመደ ሆኗል! የቁማር ጨዋታ፣ የምሽት ገበታ(night club)፣ ሆሮስኮፕ ጥንቆላ፣ ተራ ነገር ሆኗል!

ወገኖች ሆይ፣ ባለንበት ዘመን፣ የወሲብ ግንኙነት ከጋብቻ በፊት፣ ከጋብቻ ውጭ፣ ከታማኝነት ውጭ፣ ከተፈጥሮ ውጭ፣ ከሕጋዊነት ውጭ፣ ከአእምሮ ውጭ ሆኗል! ዘመድ ከዘመዱ ጋር፣ ልጅ ከእናቱ ጋር፣ ወንድም ከእህቱ ጋር፣ አባት ከልጁ ጋር፣ እንስሳ ከሰዉ  ጋር መዳራት፣ መዘሞት ተራ ነገር ሆኗል! እያገቡ–መፍታት፣ እየፈቱ–ማግባት የዘመኑ ባህል፣ የሥይጣኔው ብሂል ሆኗል!

የእግዚአብሔር ሰው ሆይ፣ አንተ እንዲህ አታድርግ! የምትኖርበት ሀገር አሕዛብ የሚያደርጉትን ርኵሰት ታደርግ ዘንድ አትማር! በአሕዛብ እርኩሰት ላይ ጌታ ይፈርዳልና እርኩሰት አትማር! የዘመኑ ሥልጣኔ ሥይጣኔ ለብሶ ዙሪያህን ቢከብብም፣ በጸሎት እየተጋህ መንፈስህን ጠብቅ! በቃሉ ብርሃን ጭለማውን እየገፈፍክ፣ በየዕለቱ በመንፈስ እየተሞላህ፣ በመንፈስ እየተመላለስክ፣ ከአንተም ከድንኳንህም እርኩሰትን አርቅ!

-------------------------
(እባክዎ፣ ይህን ዕለታዊ ዲቮሽን ላይክ ያድርጉ፣ ወዳጅ ጓደኞችዎም እንዲያገኙ ያግዙ፡፡ ጌታ ይባርክዎ!)

No comments:

Post a Comment