Saturday, November 15, 2014

የድህነት ዙፋን (#1)

ዲቮሽን ቁ.66/07     ቅዳሜ፣ ሕዳር 6/07 ዓ.ም.
(በመጋቢ ተስፋሁን ሐጢያ)


የድህነት  ዙፋን (#1)


ወንድሞች ሆይ፥እግዚአብሔር በመቄዶንያ ላሉ አብያተ ክርስቲያናት የሰጠውን ጸጋ እንድታውቁ እንፈልጋለን፡፡ …እኛ ከጠበቅነው በላይ፣ በመጀመሪያ ራሳቸውን ለጌታ ሰጡ፤ ቀጥለውም በእግዚአብሔር ፈቃድ ራሳቸውን ለእኛ ሰጡ(2 ቆሮ 8፡1-5)

በየአብያተክርስቲያኖቻችን ድህነት ዙፋኑን ዘርግቶ፣ መንግሥቱን አስፋፍቶ ይገኛል! ከዚህም የተነሳ በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ምዕመናን በጨካኙ የድህነት ቅኝ ግዛት ሥር ናቸው! ከድህነት ቀንበር ክብደት የተነሳ ምግብ፣ መጠሊያና ልብስ በመሳሰሉ መሠረተ ፍላጎቶች እጦት ይሰቃያሉ!

እስኪ አጥቢያዎቻችንን እንመልከት! በድህነት ቀንበር ሥር መሆናቸው ግልጽ ነው! እስኪ አገልግሎቶቻችንን ልብ እንበል! የማህበረ ምዕመኖቻችን የመስጠት ባሕል ቁልጭ አድርገው እንደሚያሳዩ የማያከራክር ነው! ድህነታችን ከመስጠት ባህላችን ጋር የተያያዘ ነው!
የአገልጋዮቻችን ጥራትና ብዛት፣ የስብከቶቻችን ዓይነትና ጥልቀት፣ የማምለኪያ ቦታችን ቅርጽና ይዘት፣ የንብረታችን መጠንና ግዝፈት፣ የአስተዳደራችን አመራርና ስልት፣ በአጠቃላይ በአጥቢያዎቻችን ውስጥ ያሉ ነገሮች እንኳ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከመስጠት ባሕላችን ጋር የተቆራኙ ናቸው፡፡

ታውቃላችሁ፣ በአገራችን የመስጠት ወንጌል ስላልተሰበከ የድህነት መንግሥት አልተገረሰሰም! መስጠት ስላልተሰበከ የድህነት ዙፋን አልተገረሰሰም! ከድህነት ቅኝ ግዛት ነጻ አልወጣንም!
ወገኖች ሆይ፣ መስጠት የእግዚአብሔር የሚወረስ ባህል ነው! ይህ የእግዚአብሔር ባህል በአብያተክርስቲያኖቻችን ገና አልተወረሰም! እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ሁሉን ነገር ሰጠ፡፡ የሕይወትን እስትንፋስ፣ የምንተነፍሰውን አየር፣ ውሃና ዝናብን፣ ጨረቃ ጸሐይን፣ ጤናና ሰላምን…የመሳሰሉትን ያለ ዋጋ ሰጠን! አንዲያ ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን ለኃጢአታችን ሥርየት ሰጠን! ይህም ብቻ አይደለም፣ የጌታ ልብ ዛሬም የሚያስፈልገንን ሁሉ አብዝቶ ሊሰጠን ይፈልጋል!

ታውቃላችሁ፣ እግዚአብሔር ለስጦታው ምላሽ፣ ለፍቅሩ አስታዋሽ የሚሆን የመስጠት ጸጋችን አድጎ ማየት ይሻል! የጌታ ፍላጎት በምንሰጠውና በምንዘራው መጠን የምንቀበለውና የምናጭደው እንዲበዛ ነው!

ወገኖች ሆይ፣ ቀንደኛው የበረከታችን ጠላት የሆነው ዲያብሎስ ክርስቲያኖችን በልዩ ልዩ ሽንገላዎቹ እንዳይሰጡ በትጋት እንደሚሠራ ያውቃሉ? ወገኖች ሆይ፣ ዲያብሎስ በሽንገላው በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ አማኞችን ማሳመን እንደቻለስ ያውቃሉ? መከራ–ፈተናን  የኑሮ ሁኔታን በማጋነን፣ በማካበድና አግዝፎ በማሳየትና እንዳይሰጥ በማሳመን ይሸነግላል! በሽንገላውም ብዙዎቹን ያሳምናል! በዚህም አማኞችን ከእግዚአብሔር የበረከት መስመር ውጭ ያደርጋቸዋል!

ወገኖች ሆይ፣ የመቄዶንያ አብያተ ክርስቲያናት ለዲያብሎስ ሽንገላ እጃቸውን አልሰጡም! የደረሰባቸው መከራ ጽኑ ቢሆንም፣ ደስታቸው የላቀ ነበር! ድህነታቸው ብርቱ ቢሆንም ልግስናቸው ግን የበዛ ነበር! ዐቅማቸው ትንሽ ቢሆንም ስጦታቸው ከአቅማቸው በላይ ነበር!

አንዲት ባልቴት ወገቧ ላይ ሀያ ብር ቋጥራ ወደቤተክርስቲያን ሄደች፡፡ ጌታ ከያዘችው ብር ላይ ግማሹን እንድትሰጥ ይናገራታል፡፡ ወዲያውም ዲያብሎስ ይሸነግላት ጀመር፡፡ ‹‹ያለችሽ ብር በቃ ይህቺ ናት፣ ቆጥበሽ ተጠቀሚባት እንጂ ስህተት ሰርተሽ ችግር ላይ እንዳትወድቂ›› እያለ በአእምሮ በኩል ከባድ ሙግት ገጠማት፡፡ ጌታ ረዳትና ሀያውን ብር ሰጠች፡፡

ባልቴቷ ወደቤቷ በመመለስ ላይ ሳለች፣ ዲያብሎስ አገኛትና ያሉባትን ቀዳዳዎች አጉልቶ እያሳያት ‹‹ተሳስተሻል!›› እያለ ብርቱ ሙግት ገጠማት፡፡ እርሷም ለዲያብሎስ እንዲህ ብላ መለሰችለት፣ ‹‹ተወኝ ብያለሁ፣ ቀዳዳዎቹ የራሴ፣ የሰጠሁት ለጌታዬ፣ አንተ ምን ቤት ነህ? ቅናት ይዞህ ነው እንጂ፣ አንተን የኔ ተቆርቋሪ ማን አደረገህ? እንቢ ካልክ፣ የቀረችኝን አስር ብሬን ጨርሼ እንዳልሰጥ!›› በማለት ዲያብሎስን አሳፍረውታል፡፡

ወገኖች ሆይ፣ ዲያብሎስ ከመስጠት የሚገኘውን በረከት እንዳናገኝ በብዙ መንገድ ይሸነግለናል! የድህነታችንን ጥልቀት፣ የችግራችንን ብዛት አግዝፎ እያሳየን እጃችንን ሰብስበን እንድንቀመጥ፣ ሌሎች ሲሰጡ እንድንመለከት ይሸነግለናል! የኑሮን ውድነት፣ የገቢያችንን ማነስ፣ የቤት ኪራይ፣ የልጆች ክፍያ፣ የታክሲ የወር አስቤዛ፣ የዕድር፣ የእቁብ፣ የአክሲዮን ቁጠባ እያሳየ ያስፈራራናል! በዚህም የድህነትን ዙፋን በእኛ ላይ ይጭናል!

ወገኖች ሆይ፣ የድህነትን ዙፋን መፈንቀል የምንችልባቸው ሁለት ሚስጥሮች አሉ፡፡ የመጀመሪያው ራስን ለጌታ መስጠት ነው! ሰው ራሱን አስቀድሞ ለጌታ ከሰጠ ምን ሊያስቀር ይችላል? ነፍስን ከመስጠት በላይ የሚከብድ ምን ነገር ይገኛል?

ወገኖች ሆይ፣ ከገንዘባችን በፊት፣ ከስጦታችን በፊት፣ ራሳችንን ለጌታ እንስጥ! ራሳችንን ለጌታ አስቀድመን ሰጥተን እንደሆነ መባ አስራታችንን፣ በኩራት ስጦታችንን ለጌታ ለመስጠት እጅግ ቀላል ይሆናል! መስጠት ቀላል ሲሆን የድህነት ዙፋን፣ የዙፋኑም ቀንበር፣ የቀንበሩም ክብደት በእግዚአብሔር ጉልበት ከሥር ከመሠረቱ ተነቅሎ ይጣላል!

-------------------------

(እባክዎ፣ ይህን ዕለታዊ ዲቮሽን ላይክ ያድርጉ፣ ወዳጅ ጓደኞችዎም እንዲያገኙ ያግዙ፡፡ ጌታ ይባርክዎ!)

No comments:

Post a Comment