ዲቮሽን ቁ.57/07 ሐሙስ፣ ጥቅምት
27/07 ዓ.ም.
(በመጋቢ ተስፋሁን ሐጢያ)
ዲያስፖራ (#2) – ፖለቲከኞች!
ማንኛውም ሰው በሥልጣን ላይ ላሉት ሹማምንት መገዛት
ይገባዋል፡፡ ከእግዚአብሔር ካልሆነ በቀር ሥልጣን የለምና፤ ያሉትም ባለሥጣናት ከእግዚአብሔር የተሾሙ ናቸው፡፡ ስለዚህ
በባለሥልጣን ላይ የሚያምጽ በእግዚአብሔር ሥርዓት ላይ ማመጹ ነው፡፡ ይህን የሚያደርጉትም በራሳቸው ላይ ፍርድን ያመጣሉ (ሮሜ
13፡1-3)፡፡
በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች ተበትነው የሚገኙ ሐበሻ
ዲያስፖራዎች በየጊዜው በሀገራቸው መንግሥት ፖለቲካ ላይ ከረር ያለ ተቃውሞ ያሰማሉ፡፡ ኃያላን መንግሥታት በአገራቸው መንግሥት
ላይ እርምጃ እንዲወስዱ አቤቱታቸውን ያቀርባሉ፡፡
ወገኖች ሆይ፣ የተቃውሞ ሰልፍ በማድረግ በአገራቸው መንግሥት
ላይ እርምጃ እንዲወሰድ፣ ለተራቡ ሰዎች እርዳታ እንዳይሰጥ፣ ለሚደረገው ልማት እውቅና እንዳይሰጥ የሚወተውቱት ጌታን የማውቁና
መንፈሳዊ ዓይናቸው ያልበራላቸው ሰዎች ብቻ አይደሉም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያምኑ፣ የሚሰብኩና የሚያስተምሩ፣ በክርስቶስ አምነን
ድነናል፣ ክርስቲያን ሆነናል፣ ሰማያዊ ዜጋ ሆነናል የሚሉም አሉበት፡፡
ወገኖች ሆይ፣ ታሪካቸው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሰፍሮ
የምናነባቸው ዲያስፖራዎች መንግሥታችንን አፍርሱልን፣ መሪዎቻችንን አጥፉልን፣ ለሀገራችን እርዳታ ከልክሉልን፣ ባንዲራችንን
አስወግዱልን እያሉ ኃያላን መንግሥታትን አልተማጸኑም! ይልቁንም፣ ሀገራችንን እርዱልን፣ ሕዝባችንን ጥቀሙልን፣ መንግሥታችንን
ደግፉልን፣ የሚሉ ናቸው፡፡
ወገኖች ሆይ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ‹‹ማንኛውም ሰው በሥልጣን ላይ
ላለ መንግሥት መገዛት ይገባዋል›› ካለ ክርስቲያን እግዚአብሔር ለሾመው መንግሥት፣ ለሕግና ሥርዓቱ ይገዛ እያለ ነው፡፡ መንግሥትን
የሚቃወም እግዚአብሔርን ይቃወማል፡፡ በመንግሥት ላይ የሚያምጽ በእግዚአብሔር ላይ ያምጻል፡፡ በእግዚአብሔር ላይ ማመጽ ፍርድን
ያስከትላል፡፡
ወገኖች ሆይ፣ የመንግሥታችን ሥርዓት የእግዚአብሔርን ሕግ እስካልነካ፣
በአምልኮአችን ጉዳይ ላይ ጣልቃ እስካልገባ ልንገዛለት ይገባል፡፡ ዳንኤልን አስቡ! ከአምላኩ ሕግ በቀር ለመንግሥት ታዛዥ ነው፡፡ መርዶክዮስን አስቡ! ከአምላኩ
ሕግ በቀር ለመንግሥት ታዛዥ ነው፡፡ ሲድራቅ ሚሳቅ አብደናጎን አስቡ! ለመንግሥት ታዛዥ ናቸው፡፡ ጣዖት እንዲያመልኩ፣ ለምስል
እንዲሰግዱ በአምላካቸው ሲመጡባቸው ግን አልታዘዙላቸውም!
ወገኖች ሆይ፣ ሐዋሪያ ጳውሎስ ለሮሜ ክርስቲያኖች ‹‹ማንኛውም
ሰው በሥልጣን ላይ ላለ መንግሥት መገዛት ይገባዋል›› ሲል የጻፈላቸው የሮማው ንጉሥ ኔሮ በክርስቲያኖች ላይ አሰቃቂ መከራ
ባመጣበት ወቅት ነው፡፡ ክርስቲያኖች እየታደኑ ይሰዉ ነበር፡፡ ዘይት በተሞሉ በርሜሎች እየተነከሩ እሳት ተለኩሶባቸው ከነሕይወታቸው
ለጧፍ ብርሃንነት እንዲውሉ በሚደረግበት አሰቃቂ ጊዜ ላይ የተጻፈ ነው፡፡
ወገኖች፣ ከአምላካችን ሕግ በቀር፣ በመንግሥት ላይ በሚደረጉ
የተቃውሞ ሰልፎች ላይ ክርስቲያኖች መሳተፍ የለብንም! መንግሥት በዜጎቹ ላይ ለሚፈጽማቸው ማናቸውም ክፉ ድርጊቶች በእግዚአብሔር
ይጠየቃል፡፡ ሹመትና ሽረት በእጁ ያለው ጌታ መንግሥትን ያስነሳል፣ መንግሥትን ይጥላል፡፡ የክርስቲያን ድርሻ ወደ ጌታ መጮኽ፣ ለመንግሥት
መጸለይ ነው!
ወገኖች ሆይ፣ ጸሎት ጉልበት አለው! ለዓለም ድህነት፣
ለአሕዛብ በረከት የሆኑት ኖህና አብርሃም ጸሎተኞች ናቸው! ለምድራቸው ሰላም፣ ሕዝባቸው አንድነት፣ ለመንግሥታቸው ልማት ምክንያት
የሆኑት መርዶክዮስና አስቴር፣ ዳዊትና ዳንኤል ጸሎተኞች ናቸው! ሰማይ
እንዲከፈት፣ ምድር እንዲፈወስ፣ ጣዖት እንዲደመሰስ ለማድረግ የቻሉት ኤልያስና ኤልሳዕ ጸሎተኞች ናቸው!
ወገኖች ሆይ፣ የሀገራችንን ምስል ከሚያበላሽ፣ የመንግሥታችንን
ክብር ከሚያጎድፍ፣ የሕዝባችንን ጥቅም ከሚጎዳ ማናቸውም ነገሮች እንታቀብ፡፡ በሙያችን፣ በመዋዕለ ሀብታችን፣ በጸሎታችንንና
በማናቸውም ጠቃሚ ነገራችን ከመንግሥታችን ጎን ቆመን፣ ሕዝባችንን የሚጠቅም ነገር እንሥራ! ከመወጋገዝ ይልቅ ሕዝባችንን
በሚጠቅም ነገር ላይ አብረን ብንሰማራ፣ በሀገር ልማት ላይ አብረን ብንሰራ፣ በጾምና በጸሎት እግዚአብሔርን ብንጠራ ለምድራችን ፈውስ፣
ለሕዝባችን በረከት፣ ለሀገራችን ዕድገት፣ ለፖለቲካችንም ለውጥ ይመጣል!
-------------------------
(ይህን
ዕለታዊ
ዲቮሽን
ላይክና ሼር ያድርጉ፣ ወዳጅ ጓደኞችዎም
እንዲያገኙ
ያግዙ፡፡ ጌታ ይባርክዎ!)
No comments:
Post a Comment