ዲቮሽን ቁ.67/07 እሁድ፣ ሕዳር
7/07 ዓ.ም.
(በመጋቢ ተስፋሁን ሐጢያ)
የድህነትን ዙፋን (#2)
ወንድሞች
ሆይ፥እግዚአብሔር በመቄዶንያ ላሉ አብያተ ክርስቲያናት የሰጠውን ጸጋ እንድታውቁ እንፈልጋለን፡፡ …እኛ ከጠበቅነው በላይ፣
በመጀመሪያ ራሳቸውን ለጌታ ሰጡ፤ ቀጥለውም በእግዚአብሔር ፈቃድ ራሳቸውን ለእኛ ሰጡ(2 ቆሮ 8፡1-5)
የድህነትን ዙፋን መፈንቀል
ከምንችልባቸው ሁለት ሚስጥሮች የመጀመሪያው ራስን ለጌታ መስጠት ነው! ሰው ራሱን አስቀድሞ ለጌታ ከሰጠ ለራሱ የሚሰስተው ከዚህ
የሚበልጥ ሌላ ነገር አይኖረውም! ሁለተኛው ሚስጥር ራስን ለሰው መስጠት ነው! ራስን ለሰው ስንሰጥ ለሌሎች አኗኗር እንቆረቆራለን!
መስጠት በውዴታ የሚደረግ መስዋዕት ነው! ጌታ ስጡኝ ሲል፣ የበለጠ በረከት
ሊሰጠን ነው! አብዝተን እንድንሰጥ የሚጠይቀን አብዝቶ ሊሰጠን ፈልጎ ነው! እግዚአብሔር አብዝቶ መስጠት ብቻ ሳይሆን፣ የተሻለ ነገር
ሊሰጠን ይፈልጋል! እግዚአብሔር የብዛት ብቻ ሳይሆን የጥራት አምላክ ነው! ስለሆነም፣ ያለንን ተቀብሎ የተሻለውን ሊሰጠን ይፈልጋል!
አንድ ጊዜ ስለመስጠት
ያነበብሁት ምሳሌ የሚገርም ነው! አባት ለትንሽዬ ሴት ልጁ አርቴፊሻል የአንገት ጌጥ ገዝቶላት ነበር፡፡ ልጅቱም ጌጡን በጣም ትወድደው
ነበር፡፡ ጌጡን ከገዛላት ከጥቂት ሳምንታት በኋላ አባት ልጁን ትወድደው እንደሆነ ጠየቃት፡፡ ልጅትም ሕጻናት እንደሚያደርጉት ሁሉ
በአባቷ ጉንጮች ላይ ለደቂቃዎች ተጣብቃ እየሳመችው ፍቅሯን ገለጸችለት፡፡
አባትም ቀጠል አድርጎ
በጣም ትወድደው ከሆነ ያንን በጣም የምትወድደውን ጌጥ እንድትሰጠው ልጅቱም ደንግጣ ዓይን ዓይኑን እያየች ዝም አለች፡፡ አባት አሁንም
ልጁን ጌጠን እንድትሰጠው ጠየቃት፡፡ እርስዋ ግን በጣም ተጨናነቀች፡፡ ጭንቀትዋም ሲበዛ ዓይንዋ እያየ ልትሰጠው ስላልፈገች ፊቷን
ዞራ በሐዘን በተሰበረ መንፈስ ጌጡን ከአንገትዋ አውልቃ ለአባትዋ ወረወረችለት፡፡
አባትዋም አርቴፊሻል
ጌጡን ዓይኗ እያየ በጣጥሶ ከፊትዋ በተነላት፡፡ ይኼኔም ልጅት ለቅሶዋን አፈነዳችው፡፡ ለቅሶዋ እንዳቧራ አባት እጁን ከኪሱ ከተተና
የወርቅ ሀብል አውጥቶ በአንገትዋ አጠለቀላት!
ወገኖች ሆይ፣ አንዳንዴ
እኛንም የዚህ ዓይነት ችግር ይፈታተነናል! እግዚአብሔር በእጃችን ያለውን ነገር ተቀብሎ
በእጁ ያለውን የከበረ ነገር ሊሰጠን ሲፈልግ ለመወሰን እንጨናነቃለን!
ወገኖች ሆይ፣ ገንዘብ ኃላፊ፣ ጠፊ ነው! ከእናታችን ማህጸን የወጣነው ራቁታችንን፣
ባዶ እጃችንን ነው–ስንሞትም የምንሄደው ሁሉን ጥለን ነው! ብልህነት ይህን ሚስጥር ማወቅ ነው! አስተዋይነት በሚያልፍና በሚጠፋ
ገንዘብ የማያልፈውንና የማይጠፋውን መዝገብ በእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ ማኖር ነው! ብልህነት ለጌታ መስጠት ነው! ለጌታ ስንሰጥ ብልና
ዝገት በማያጠፉት፣ ሌቦች ቆፍረው በማይሠርቁት በሰማይ መዝገብ ላይ ሀብትን መሰብሰብ ነው!
ወገኖች ሆይ፣ ብልጽግና ከንቱ፣ ሀብትም ጊዜያዊ ነው! ለዓመታት ደክመን ያፈራነው ጥሪት ከሞትን
በኋላ በጥቂት ወራቶች የሚደመሰስ ነው! ይህን እውነት አውቀን እንድንመላለስ፣ እግዚአብሔር ይርዳን! ‹‹አንዱ ቁራሽ አጥቶ
ተደፍቶ ሲያድር፣ ግማሻችን ተርፎን ስንደፋ በምድር፣ ከዚህ ጨካኝነት ጌታ ይፈውሰን፣ ሩህሩህ የሆነውን የራሱን ልብ ይስጠን!››
(ተፈጸመ)
-------------------------
(እባክዎ፣ ይህን
ዕለታዊ
ዲቮሽን
ላይክ ያድርጉ፣
ወዳጅ ጓደኞችዎም እንዲያገኙ ያግዙ፡፡ ጌታ ይባርክዎ!)
No comments:
Post a Comment