Friday, October 24, 2014

አባናና ፋርፋ !

ዲቮሽን ቁ.44/07     አርብ፣ ጥቅምት 14/07 ዓ.ም.
(በመጋቢ ተስፋሁን ሐጢያ)


አባናና ፋርፋ !

…የደማስቆ ወንዞች አባናና ፋርፋ ከእስራኤል ውኆች ሁሉ አይሻሉምን? በእነርሱስ ውስጥ መታጠብና መንጻት አይቻለኝም ኖሮአልን? ዘወርም ብሎ ተቈጥቶ ሄደ…ባሪያዎቹም ቀርበው። አባት ሆይ፥ ነቢዩ ታላቅ ነገርስ እንኳ ቢነግርህ ኖሮ ባደረግኸው ነበር ይልቁንስ። ታጠብና ንጹሕ ሁን ቢልህ እንዴት ነዋ! ብለው ተናገሩት። ወረደም፥ የእግዚአብሔርም ሰው እንደ ተናገረው በዮርዳኖስ ሰባት ጊዜ ብቅ ጥልቅ አለ ሥጋውም እንደ ገና እንደ ትንሽ ብላቴና ሥጋ ሆኖ ተመለሰ፥ ንጹሕም ሆነ…(2 ነገ 5፡6-15)

ታውቃላችሁ፣ ብዙ ጊዜ የእግዚብሔርን ሐሳብ በራሳችን ማስተዋል እንገመግምና ውድቅ እናደርጋለን! በዚህም ከሕመማችን ሳንፈወስ፣ ያሰበልንን ሳንወርስ፣ ወዳየልንም ሳንደርስ እንቀራለን!

ታውቃላችሁ፣ ጌታ የሚናገረን ነገር ከልማዳችን ውጭ የሆነ እንደሆነ፣ ከእይታችን ውጭ የሆነ እንደሆነ፣ ከክልላችን ውጭ የሆነ እንደሆነ …ለመቀበል እንቸገራለን! ጌታ የተናገረን ከባህላችን ውጭ የሆነ እንደሆነ፣ ከቋንቋችን ውጭ የሆነ እንደሆነ፣ ከብሔራችን ውጭ የሆነ እንደሆነ፣ ከእውቀታችን ውጭ የሆነ እንደሆነ፣ …ለመታዘዝ እንቸገራለን!

ወዳጄ ሆይ፣ ጌታ ለእርስዎ የሚረባዎትንና የሚበጀዎትን ነገር ያውቃል! ስለሆነም ‹‹አድርግ!›› ያለዎት ነገር ከግምትዎም ከእቅድዎም ውጭ ቢሆን ይታዘዙ!

ወዳጄ ሆይ፣ ጌታ የሚነግርዎት የሚጠቅምዎትን ነው! የሚናገርዎት ነገር አድካሚ ቢመስል፣ አስቸጋሪም ቢሆን ታዘውት ይፈጽሙ!

ወዳጄ፣ ጌታ የተናገረዎ፣ ለክብርዎ ባይመጥን፣ ለደረጃዎ ባይሆን፣ የማይሆን ቢመስል፣ ፈተና ነውና ጌታን ይታዘዙት! ‹‹አድርግ›› ያለዎትን ነገር ታዝዘው ይፈጽሙ!

ወዳጄ ሆይ፣ እግዚአብሔር ታዝዞ ከከፍታ መውረድ፣ ከክብር መዋረድ የለምና ያለዎትን ያድርጉ! እርሱን በመታዘዝ ከደረጃ ማነስ፣ ከቁጥር መቀነስ የለምና ያለዎትን ያድርጉ! እርሱን በመታዘዝ ከበረከት በደል፣ ከሙላት መጓደል የለምና ያለዎትን ያድርጉ!

ወዳጄ ሆይ፣ ጌታ ሲናገርዎ ከሀገርዎም ውጭ ቢሆን፣ ከወንዝዎም ውጭ ቢሆን ድምጹን ሰምተው፣ እርሱን ታዝዘው ይፈጽሙ! ጌታን ሲታዘዙ ፈውሱን በረከቱን፣ ደስታና ሐሴቱን፣ ከፍታ ጥልቀቱን ወርድና ስፋቱን የመለኮት ሙላቱን ይወርሳሉ!


-------------------------
(ይህን ዕለታዊ ዲቮሽን ላይክና ሼር ያድርጉ፣ ወዳጅ ጓደኞችዎም እንዲያገኙ ያግዙ፡፡ ይህን አገልግሎት ለመደገፍ (Tesfahun Hatia Daka, Commercial Bank of Ethiopia, Andinet Branch; A/C 1000036318949; Swift Code: CBETETAA) መላክ ትችላላችሁ፡፡ ለዘሪ ዘርን የሚሰጥ ጌታ ዘራችሁን ይባርክልኝ!)

No comments:

Post a Comment