Thursday, October 23, 2014

በትዕግሥት ይሩጡ !

ዲቮሽን ቁ.43/07     ሐሙስ፣ ጥቅምት 13/07 ዓ.ም.
(በመጋቢ ተስፋሁን ሐጢያ)


በትዕግሥት ይሩጡ !

…እንግዲህ እነዚህን የሚያህሉ ምስክሮች እንደ ደመና በዙሪያችን ካሉልን፥ እኛ ደግሞ ሸክምን ሁሉ ቶሎም የሚከበንን ኃጢአት አስወግደን፥የእምነታችንንም ራስና ፈጻሚውን ኢየሱስን ተመልክተን፥ በፊታችን ያለውን ሩጫ በትዕግሥት እንሩጥ፤ እርሱ ነውርን ንቆ በፊቱም ስላለው ደስታ በመስቀል ታግሦ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ ተቀምጦአልና (ዕብ 12፡1-2)


ታንዛኒያዊው ጆን ስቲፈን የ1968ቱን የሜክሲኮ ሲቲ ኦሎምፒክ ማራቶን ላይ እነማሞ ወልዴን ጨምሮ ከ75 አትሌቶች ጋር ይሮጥ ነበር፡፡ በ2:20:26  ሰዓት በማሞ ወልዴ አሸናፊነት የተጠናቀቀውን የዕለቱን ሩጫ መጨረስ የቻሉት 57 ሯጮች ብቻ ናቸው፡፡
ከዕለቱ ሯጮች መካከል የመጨረሻው ፈጻሚ ታንዛኒያዊው ጆን ስቲፈን ሲሆን የፍጻሜ መስመሩን ያቋረጠው በ3:25:27 ሰዓት ላይ ነው፡፡


ይህ ሰዓት ለዕለቱ አሸናፊዎች ሜዳሊያ ተሰጥቶ፣ ተመልካቾች ወደቤታቸው መሄድ የጀመሩበት ሰዓት ስለሆነ በስቴዲዮሙ የቀሩት በጥቂት ሺዎች የሚቆጠሩ ብቻ ናቸው! የዕለቱ የሜዳሊያ ሥርዓት የሚቀርጹ የቴሌቪዥን ጋዜጠኞችም አካባቢውን ለቅቀው ነበር፡፡ ይሁንና በ1968ቱ የሜክሲኮ ሲቲ ኦሎምፒክ ማራቶን ላይ ሁራ የወጣ ጆን ስቲፈን በዚህ ማራቶን ላይ ብቻ ሳይሆን በዓለም የታሪክ መዝገብ ላይ በአስተማሪነቱ ከፍ ያለ በወርቅ ቀለም የተጻፈ ታሪክ ማስተላለፍ ችሎአል፡፡


ጆን ስቲፈን የ42 ኪሎሜትሩን ውድድር ጀምሮ ወደ 19ኛው ኪሎሜትር ላይ ሲደርስ ለሜዳሊያ ይሮጡ ከነበሩ ሌሎች አትሌቶች ጋር ተጋጭቶ ወደቀ፡፡ በጉልበቱ ላይ ክፉኛ ስለተጎዳ ከመቁሰሉም በላይ የጉልበቱ ጅማት ተላቅቆ ነበር፡፡ ትከሻውም በትራኩ ጠርዝ ከፉኛ ተጎድቶ ነበር፡፡ ሆኖም ጆን ስቲፈን እንዲህ የመሰለ ከባድ አደጋ ቢደርስበትም ከወደቀበት ተነስቶ ሩጫውን ቀጠለ፡፡ 

ደሙ እየፈሰሰ፣ ሕመሙ እያሰቃየው ሳያቋርጥ በደከመና በዛለ ጉልበቱ እየተወላገደ ከስቴዲዮሙ ሲገባ ያልተጠበቀ የስቴዲዮሙ ጠሩንባ ጩኸት ተሰማ! የስቴዲዮሙን ሳይረን ተከትሎም በስቴዲዮሙ የነበረው በጥቂት ሺዎች የሚቆጠር ተመልካች ቆሞ በፉጨት፣ በጩኸትና በጭብጨባ ጆን ስቲፈን ደማቅ በሆነ ሁኔታ ተቀበለው! የፍጻሜ መስመሩን ሲያቋርጥም ጋዜጠኞች እንዲህ ዓይነት ጉዳት ደርሶበት ለምን ሩጫውን እንዳላቋረጠ ሲጠየቅ እንዲህ ብሎ መለሰ፡፡ ‹‹ሀገሬ ከ5ሺ ማይልስ ርቀት ወደዚህ የላከችኝ ሩጫውን አቋርጬ እንድወጣ ሳይሆን የጀመርኩትን ሩጫ እንድፈጽም ነው!›› በማለት መላው ዓለምን የሚያስተምር ምላሽ ሰጥቷል፡፡


ወዳጄ ሆይ፣ እግዚአብሔር የጠራዎ የሕይወትን ሩጫ እንዲጀምሩ ብቻ ሳይሆን
እንዲፈጽሙ ነው! በሕይወት ሩጫ ላይ መውደቅና መነሣት፣ መቁሰልና መድማት ቢኖርም በትዕግሥት እየሮጡ እንዲፈጽሙ ነው! በዚህች ዓለም መኖር ብዙ ጉዳት አለው፡፡ ይህችን ዓለም ክደን ጌታን በመከተል ሩጫ ስንጀምር ተግዳሮት ይበዛል፡፡ የሚያደናቅፈው፣ ጠልፎ የሚጥለው፣ ጥሎ የሚሰብረው፣ ሰብሮም የሚገድለው ብዙ ነው!


ወዳጄ ሆይ፣ በሕይወት ሩጫ ላይ በሆነ አጋጣሚ ተደናቅፈው ወድቀው ይሆናል! ወድቀውም ተሰብረው ይሆናል! ስብራትዎትም የማይፈወስ መስሎ ይታይዎት ይሆናል! ወዳጄ ሆይ፣ ሀገርዎ በሆነችውን መንግሥተ ሰማያትን ያስቡ! ጌታን ተቀብለው የሕይወትን ሩጫ ለመጀመር ውሳኔ ባደረጉባት በዚያች ቅጽበት መላዕክት በደስታ በጭብጨባ በእልልታና በፉጨት ደስታቸውን ገልጸዋል!


ሰማያዊ አገርዎትን ወክለው በዚህች ዓለም ውስጥ የሕይወት ሩጫ ሲጀምሩ ሩጫውን ጨርሰው ወደ አገርዎ በክብር እንዲገቡ ይጠበቅብዎታል! ወድቀው ቢሰበሩም፣ የወደቁ ይነሣሉና በዚህ ተስፋ አይቁረጡ! በሕይወት ሩጫ ላይ መስመሩን የሳቱ ይመለሳሉና ተስፋ አይቁረጡ! ምሕረቱ ለዘላለም ናትና፣ በሕይወት ሩጫ ላይ ኃጢአት ሠርተውም ቢሆን አይዞዎት! ጻድቅ ሰባት ጊዜ ወድቆ ሰባቴ ይነሣልና፣ በወደቁበት ተስፋ ቆርጠው አይቅሩ! ከወደቁበት ተነስተው ሩጫ ይቀጥሉ!


ወዳጄ ሆይ፣ ምሕረቱ አያልቅምና በሕይወት ሩጫ ላይ በሚያጋጥም ፈተና፣ በውድቀት፣ በመከራ፣ በችግር ምክንያት አቋርጠው አይውጡ! የሚራራልዎ አምላክ አለ! በድካምዎ የሚረዳዎት ጌታ አለ! ስለሆነም፣ ሩጫዎትን በትዕግሥት ይሩጡ !

-------------------------

(ይህን ዕለታዊ ዲቮሽን ላይክና ሼር ያድርጉ፣ ወዳጅ ጓደኞችዎም እንዲያገኙ ያግዙ፡፡ ይህን አገልግሎት ለመደገፍ (Tesfahun Hatia Daka, Commercial Bank of Ethiopia, Andinet Branch; A/C 1000036318949; Swift Code: CBETETAA) መላክ ትችላላችሁ፡፡ ለዘሪ ዘርን የሚሰጥ ጌታ ዘራችሁን ይባርክልኝ!)

No comments:

Post a Comment