ዲቮሽን ቁ.26/07 ሰኞ፣
መስከረም 26/07 ዓ.ም.
(በመጋቢ ተስፋሁን ሐጢያ)
ሞገስ እንዲኖርህ …!
እግዚአብሔርም የሰው
ክፉት በምድር ላይ እንደ በዛ፥ የልቡ አሳብ ምኞትም ሁልጊዜ ፈጽሞ ክፉ እንደ ሆነ አየ። እግዚአብሔርም
ሰውን በምድር ላይ በመፍጠሩ ተጸጸተ፥ በልቡም አዘነ። እግዚአብሔርም፦ የፈጠርሁትን ሰው ከምድር ላይ አጠፋለሁ፥ ከሰው እስከ
እንስሳ እስከ ተንቀሳቃሽም እስከ ሰማይ ወፍም ድረስ ስለ ፈጠርኋቸው ተጸጽቼአለሁና አለ። ኖኅ ግን በእግዚአብሔር ፊት ሞገስን
አገኘ። የኖኅ ትውልድ እንዲህ ነው። ኖኅም በትውልዱ ጻድቅ ፍጹምም ሰው ነበረ ኖኅ አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር አደረገ (ዘፍ
6፡5-9)
እንደ ኖህ ዘመን ሁሉ፣ የትውልዳችን ክፋት በዝቷል! ጠፍቷል! በትውልዱ አናት ላይ ሰይጣን ዙፋን ተክሏል! በቤተክርስቲያን ውስጥም ኃጢአት ምሽግ ሰርቷል! ማግባትና መፍታት፣ የተፋታን ማግባት ተራ ነገር ሆኗል፡፡ ምንዝርነት፣ እርኩሰት፣ ዓለማዊ ምኞት ሲበዛ ተለምዷል፡፡ የአማኝ አላማኝ ልዩነቱ ቀርቷል! ቅድስና ጽድቁ መላ ቅጡ ጠፍቷል! ነገረ ስራችን ውጥንቅጡ ወጥቷል!
የዘመናችን ቤተክርስቲያን
ግብረሰዶማዊያንን በተክሊል እያጋባች ነው፡፡ በበርካታ አገልጋዮችና መሪዎች ዘንድ ሳይቀር እግዚአብሔርን መፍራት እንደ ኋላቀርነት እየተቆጠረ ነው፡፡ ሳይጋቡ መዘሞት እየቀለለ
ነው፡፡ ስርቆቱ፣ ሙስናው፣ ዝርፊያውና ንጥቂያው እየጨመረ ነው፡፡
እንደ እኛ ዘመን ሁሉ፣
የኖህ ዘመን ትውልድ በኃጢአት የተበከለ
ነበር፡፡ የልባቸው ክፋትና የኃጢአታቸው ክርፋት ምድርን አበላሸ፡፡ በዘመኑ ሰዎች ኃጢአት ምክንያት በተፈጥሮ ላይ ሳይቀር ቀውስ
ደረሰ፡፡
እግዚአብሔር በዘመኑ
ከሚኖሩ ሰዎች መካከል ፈልጎ ያገኘው ኖኅን ብቻ ነበር፡፡ ኖህ በትውልዱ መካከል በልዩነት ይመላለስ ነበር፡፡ ከትውልዱ አካሄድ እራሱን
ለይቶ፣ ከዘመኑ ሩጫ መንፈሱን ገትቶ ነበር፡፡ ትውልዱ ሲፋንን እርሱ ለጽድቅ ተገዝቶ ነበር፡፡ ሕዝቡ ሲበላ ሲጠጣ፣ ሊዘፍን ሲነሳ፣
ሲያገባ ሲፈታ፣ ኖህ ግን ልዩነት ነበረው፡፡
የኖህ ዘመን ትውልድ
ጸበሉ ጸዲቁ፣ ፌሽታና ድግሱ፣ ዳንስና ዘፈኑ በምድሩ ላይ ሲበዛ ሰዎች አላወቁም፡፡ ሲበሉ ሲጠጡ፣ ሲያገቡ ሲፈቱ በጊዜ አልነቁም፡፡
የኃጢአት ዳንኪራ፣ የጭፈራና እልልታ ጩኸት በምድሪቱ ሲበዛ ሁሉ ሰላም መስሎ ነበር፡፡ እግዚአብሔር በእነዚህ ሁኔታዎች የማያገባው፣
ቸል ያለ፣ ዝም ያለ፣ መሰላቸው፡፡ ነገር ግን በድንገት የጥፋት
ውኃ መጥቶ ሁሉንም ወሰዳቸው! ከኃጢአት ክርፋታቸው ጋር ከምድር ገጽ ላይ ጠርጎ
አጠፋቸው!
ዛሬም የኛ ትውልድ ይኼው
መጥቶበታል! በኃጢአታችን ምክንያት ምድር ተበላሽታለች፡፡ ሽብርተኝነቱ፣ የእርስ በርስ ጦርነቱ፣ የደም መፋሰሱ… በየቦታው በዝቷል፡፡
በኃጢአታችን ምክንያት ተፈጥሮ ተቃውሷል፡፡ የአየር ብክለት፣ የእሳተ ገሞራዎች ፍንዳታ፣ የጎርፍ መጥለቅለቅ፣ የአውሮፕላኖች መከስከስ፣
የመርከቦች መስጠም … ይጠቀሳል፡፡ ድርቅና ረሃብ፣ ቀሳፊ ደዌዎችም እየበረከቱ ነው፡፡
ይህ ብቻም አያበቃም!
አንድ ቀን በድንገት ጌታችን ኢየሱስ በሕያንና በሙታን ሊፈርድ በመላዕክት ታጅቦ በደመና ይመጣል፡፡ የተዉት፣ የካዱት፣ የናቁት ያዩታል!
በኖኅ ዘመን እንደሆነው፣ ሰዎች ሲበሉ ሲጠጡ፣ ሲያገቡ ሲጋቡ ሳለ የጥፋት ውኃ ድንገት እንደመጣ፣ ጌታችን በድንገት ይመጣል፡፡ ለያንዳንዱም እንደ ስራው
ዋጋውን ይሰጣል!
የእግዚአብሔር ሰው ሆይ፣
ምድር እንዳትጠፋ እግዚአብሔርን ፍራ! በትውልድህ መካከል በጽድቅ ተመላለስ! ከትውልድህ መካከል ፈልጎ እንዲያገኝህ፣ በፊቱም ሞገስ
እንዲኖርህ፣ አካሄድህን ከእግዚአብሔር
ጋር አድርግ!
(ይህን ዕለታዊ ዲቮሽን ላይክ እና ሼር ያድርጉ፣ ወዳጅ ጓደኞችዎም እንዲያገኙ ያግዙ፡፡ ዲቮሽኑ ሳይቋረጥ ዓመቱን ሙሉ እንዲቀጥል በጸሎትዎና ጌታ በልብዎ በሚያስቀምጥ ማናቸውም ነገር ሁሉ ይደግፉ፡፡ ጌታ ይባርክዎ፡፡)
No comments:
Post a Comment