ዲቮሽን ቁ.39/07 እሁድ፣ ጥቅምት
9/07 ዓ.ም.
(በመጋቢ ተስፋሁን ሐጢያ)
በሰው አንታመን !
በፋሲካ በዓልም በኢየሩሳሌም ሳለ፥ ያደረገውን ምልክት ባዩ ጊዜ ብዙ ሰዎች በስሙ አመኑ፤ ነገር ግን ኢየሱስ
ሰዎችን ሁሉ ያውቅ ነበር፤ ስለ ሰውም ማንም ሊመሰክር አያስፈልገውም ነበርና አይተማመናቸውም ነበር፤ ራሱ በሰው ያለውን ያውቅ
ነበርና (ዮሐ 2፡23-25)
ብዙ ጊዜ ሰዎችን በሆነ ነገራቸው እናውቃቸውና እንሸወዳለን! ሰዎች ክፉ
ሲሠሩ አይተን እንጠላቸዋለን፣ መልካም ሲሠሩ ደግሞ እንወዳቸዋለን! ሲዘፍኑ አይተን እንርቃቸዋለን፣ ሲዘምሩ አይተን እንቀርባቸዋለን!
ቤተክርስቲያን ከማይመጡት እንሸሻለን፣ ቤተክርስቲያን ከሚመጡት እንቀርባለን! በጌታ ያልሆነውን እንጠረጥራለን፣ በጌታ የሆነውን
እናምናለን! በዚህም እንሸወዳለን!
ጉድና ጅራት ወደኋላ ነውና፣ የሰው እውነተኛ ማንነት የሚታወቀው
ሲተዋወቁ ሳይሆን፣ አብረው ሲቆዩ ነው! ሰው ውስጡ የማይታወቅ ፍጡር ነው! የሰውን እውነተኛ ማንነት ለማወቅ በጣም ያስቸግራል!
ብዙ ሰው የውስጥ ማንነቱ ቆሻሻ ነው! ነገር ግን እንዳይታወቅበት ጭንብል ይለብሳል!
ታውቃላችሁ፣ ሐዋርያውም፣ መጋቢውም፣ ነቢይ ወንጌላዊው፣ መምህር ዘማሪው፣
ዲያቆን ሽማግሌው … ሁሉም ሰዎች ናቸው! ቀርበን ብናያቸው፣ እውነተኛውን ማንነታቸውም የሚደብቁበት የየራሳቸው ጭንብል አላቸው!
መምሰል አቅቷቸው፣ መሆን ተስኗቸው፣ የሚያስመስሉበት መንገድ አላቸው! አርቴፊሻል ሕይወት ይዘው፣ ሰው ሠራሽ ድራማ ሠርተው፣
በሰው ፊት ወጥተው በድንቅ የሚተውኑበት ምርጥ ብቃት አላቸው! በዚህ እንሸወዳለን!
ታውቃላችሁ፣ ሰው አስመሳይ ነው! ወዳጅ መስሎ ጠላት ይሆናል! በማር ውስጥ ደብቆ እሬት ያበላል! ጽድቅ
መስሎ ኃጢአት ይሠራል! በልጅ አመኻኝቶ አንጉቶ ይበሏል! የበግ ለምድ ለብሶ ተኩላ ይሆናል! በጥርሱ እያሳቀ በልቡ ያደማል!
እያጨበጨበልን፣ ሆ!ሆ! እያለልን፣ ጉድጓድ ይቆፍራል! ጠልፎ መጣያ ገመድ፣ የማሰናከያ ወጥመድ ይዘረጋል!
ወገኖች ሆይ፣ ጌታ ኢየሱስ ግን ሰውን ያውቃል! ልብ ያሰበውን፣ ኩላሊት
ያመላለሰውን ሁሉ ያውቃል! ስለሆነም፣ ሰዎችን በማንነታቸው ጠንቅቆ ስለሚያውቅ፣ የሚሉትን ሳይሆን ውስጣቸውን ያነብባል! ሰዎች ‹‹ሆሣዕና፣
ሆሣዕና›› እየተባለ በተጮኸለት ማግሥት ‹‹ስቀለው፣ ስቀለው›› እንደሚከተል ያውቃል! ከሕዝቡ አብዛኛው ልብሱን መሬት ላይ
እያነጠፈ፣ የዛፍ ቅጠሎች እየዘነጠፈ እንኳን የእርሱ፣ የአህያው እግር መሬት እንዳይረግጥ ምንጣፍ እየሠሩ፣ ፊትና ኋላውን
ከብበው ‹‹ሆ፣ ሆ›› እያሉ በዘመሩለት በዚያው ምድር፣ ቀንበር አሸክመውት፣ እሾኽ ጎንጉነውበት፣ እየገረፉትና እየረገሙት እያዳፉትና
መሬት ለመሬት እየጎተቱት እንደሚያሰቃዩት አያውቃል! ልብሳቸውን ባነጠፉለት ማግሥት ልብሱን እንደሚገፉት፣ ዕጣ እንደሚጣጣሉበት
ያውቃል!
ወገኖች ሆይ፣ ጌታ ሰውን ያውቃል! ‹‹ከአንተ ወደ ማን እንሄዳለን?››
ብለው የነገሩት ጥለው እንደሚሸሹት፤ ‹‹አልክድህም›› ያሉ ‹‹አላውቀውም›› እያሉ ምለው እንደሚገዘቱ፣ ‹‹ሰላም ላንተ ይሁን››
ብለው ሰላሙን እንደሚያናጉ፣ … ያውቃል!
‹‹በጌታ ስም የመጣ የተባረከ ነው›› ባሉበት አንደበት ‹‹የተረገመ
ነው›› ብለው እንደሚጮኹ ያውቃል!
ታውቃላችሁ፣ ጌታችን ኢየሱስ የሰዎችን እውነተኛ ማንነት ስለሚያውቅ
ማንም ስለሰው እንዲመሰክርለት አያስፈልገውም ነበር፡፡ የቤተክርስቲያን አባልነት፣ የመልቀቂያ ጽህፈት፣ የምስክር ወረቀት
አይጠይቅም! ሁሉንም ያውቃልና!
ታውቃላችሁ፣ በምስክር ወረቀታቸው የተቀበልናቸው፣ ሴቶች ልጆቻችንን ያጋባናቸው፣
ጉድና ጅራታቸው ከኋላ የታየባቸው ብዙ ናቸው! እምነት ጥለው ክህደት የፈጸሙ፣ ትዳር ፈትተው ቤተሰብ የበተኑ፣ ገንዘብ ዘርፈው
ኮቴያቸውን ያጠፉ አሉ!
ወገኖች ሆይ፣ ጌታ በሰዎች አልታመነምና እኛም እንጠንቀቅ! ሰውን
መውደድ እንጂ፣ ሙሉ በሙሉ አንታመንባቸው! በሰው ልጆች ላይ ሙሉ እምነት ጥለን አንደገፍባቸው! ምርኩዙ ተሰብሮ ወድቀን
እንዳንሰበር ጥንቃቄ እናድርግ! በችኮላ አምነን፣ በችኮላ ወድደን፣ ቸኩለን አግብተን፣ ኋላ እንዳንሰበር ጥንቃቄ እንውሰድ! መከራ
ካልመጣ፣ ገበና ካልወጣ፣ የሰው ማንነቱ አይታወቅምና በሰው አንታመን! ሁሉን አስተውለን በጥበብ አናድርግ!
------------- -------------
ማስታወቂያ፣
(1) ጌታ ቢፈቅድ፣ ከመስከረም 1
እስከ ሕዳር 30/07 ያለው ዕለታዊ ዲቮሽን በመጽሐፍ ታትሞ ኢንተርኔት ለማይጠቀሙ ሐበሾች የማድረስ ራዕይ አለኝ፡፡ ስለሆነም፣
ይህን ራዕይ በገንዘብ በመደገፍ አገልግሎቱን ለማሳደግ ልባችሁ የተነሳሳ ወገኖች አነሰ በዛ ሳትሉ የእምነት ዘር በመዝራት ከጎኔ
እንድትቆሙ በጌታ ፍቅር እጠይቃለሁ፡፡ የፍቅር ስጦታችሁን (Tesfahun Hatia Daka, Commercial Bank of
Ethiopia, Andinet Branch; A/C 1000036318949; Swift
Code: CBETETAA) በማለት መላክ ትችላላችሁ፡፡ ለዘሪ ዘርን የሚሰጥ ጌታ ዘራችሁን ይባርክ!
(2) ጌታ ቢፈቅድ ከአዲሱ የፈረንጆች ዓመት
2015 ጀምሮ፣ ከአማርኛው ዕለታዊ ዲቮሽን በተጨማሪ፣ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ዕለታዊ ዲቮሽን እጀምራለሁ፡፡ ይህ አገልግሎት በመላው
ዓለም የሚገኙ የእንግሊዝኛ ቋንቋ የሚግባቡትን ሁሉ ለመድረስ ኢላማ ያደረገ ነው፡፡ ስለሆነም፣ በጸሎታችሁ እንድታስቡኝ በጌታ
ፍቅር አደራ እላለሁ፡፡
(3) ‹‹የወንጌላዊው እጮኛ›› በሚል ርዕስ የተዘጋጀና በወንጌል አገልጋዮች
ላይ የሚያጋጥሙ እውነተኛ ልብ አንጠልጣይ ታሪኮችን አሰባስቦ የያዘ መጽሐፍ ጌታ ቢፈቅድ በዚህ ወር መጨረሻ ላይ ለንባብ
ይበቃል፡፡ ይህን መጽሐፍ በመግዛት ዕለታዊ ዲቮሽኑን እንድትደግፉ በአክብሮት እየጠየቅሁ፡፡ በአገር ውስጥ ያላችሁም ሆነ ከአገር
ውጭ መጽሐፉን በመን መንገድ ልልክላችሁ እንደምችልም መረጃ እንድትሰጡኝ በአክብሮት አሳስባለሁ፡፡ የመጽሐፉ መሸጫ ዋጋ
በሚቀጥለው ሳምንት ይፋ ይሆናል! ጌታ ይባርካችሁ!
No comments:
Post a Comment