ዲቮሽን ቁ.40/07 ሰኞ፣ ጥቅምት
10/07 ዓ.ም.
(በመጋቢ ተስፋሁን ሐጢያ)
እስኪ እናመስግን!
በመንፈቀ ሌሊት ግን ጳውሎስና ሲላስ እየጸለዩ እግዚአብሔርን በዜማ
ያመሰግኑ ነበር፥ እስረኞቹም ያደምጡአቸው ነበር፡፡ ድንገትም የወኅኒው መሠረት እስኪናወጥ ድረስ ታላቅ የምድር መንቀጥቀጥ ሆነ፤
በዚያን ጊዜም ደጆቹ ሁሉ ተከፈቱ የሁሉም እስራት ተፈታ (የሐዋ 16፡25-26)።
ጳውሎስና ሲላስ እንደ ደረሰባቸው የድብደባና እስራት ከባድነት ማመስገን የሚችሉበት ሁኔታ አልነበረም!
ልብሳቸው ተገፍፎ፣ ራቁታቸውን ነው በሽመል የተደበደቡት! ራቁት ሰውነት በደረቅ በትር ሲደበደብ ከባድ ጉዳት ይደርሳል! ይቆስላል፣
ይደማል! ይህም ብቻ አይደለም፣ ወደ ወኅኒ ቤት ውስጠኛው ክፍል ተጥለው፣ እግራቸው ከግንድ ጋር ተጣብቆ ታስሯል! ከባድ ፈተና ነበር
ያጋጠማቸው!
ነገር ግን ጳውሎስና ሲላስ በደረሰባቸው ከባድ ፈተና ምክንያት ሞራላቸው ወድቆ፣ ተስፋቸው ሞቶ
በጌታ ላይ ሲያማርሩ አናይም! ይልቁንም ያልታጠበ ደማቸው እየተንዠቀዠቀ፣ ያልታከመ ቁስላቸው እየጠዘጠዛቸው፣ የግርፋቱ ሕመም እያሰቃያቸው
ባለበት ሁኔታ፣ በደረቀ ጉሮሮአቸውና በደከመ ድምጻቸው ጌታን በዝማሬ ሲያመሰግኑ እናያለን!
ወዳጄ ሆይ፣ በሕይወትዎ፣ በኑሮዎ፣ ወይንም በማናቸውም ማኅበራዊ ግንኙነትዎ የተገረፉበት፣
የተጎዱበት፣ የቆሰሉበትና የደሙበት ነገር ይኖር ይሆን? ስለጌታ ብለው የተገፉበት፣ የተወገዙበት፣ የተጠሉበትና የተገለሉበት ነገር
ይኖር ይሆን? እስኪ ማመስገን ይጀምሩ!
ታውቃላችሁ፣ መስቀል ተሸክመን፣
በመከራ ተከብበን፣ ከነቁስላችንና ከነምርቅዛችን፣ ከነሕመማችንና ከነራስ ምታታችን ወደ ጌታ ቀርበን ከክብሩ ዙፋን ሥር ምስጋና ስንሰዋ
እግዚአብሔር ይነሣል! እግዚአብሔር ሲነሣ ጠላት ይሸበራል! ጠላታችን ሲሸበር ቀንበር ይሰበራል! ቀንበሩ ሲሰበር እስራት ይፈታል!
እስራት ሲፈታ እግዚአብሔር ይከብራል!
ወገኖች ሆይ፣ ጌታ በመከራችን ፍጹም አይደሰትም! መልካም አባት ነውና፣ ዳቦ ስንለምነው ድንጋይ
አይሰጠንም! እያለቀስንበት እንደ መልካም አባት በፍቅር ቃል እያባበለ፣ ያጽናናናል እንጂ ፊቱን አያዞርም! መከራን ተጠቅሞ፣ ክብሩን
ይገልጣል እንጂ ጌታ ዝም አይልም! ስለሆነም፣ እስኪ ከነቁስላችን ከነሕመማችን፣ ከነራስ ምታታችን ጌታን እናመስግን!
ወገኖች ሆይ፣ እስኪ እናመስግን! ትናንትና አልፎ ዛሬን ደርሰናልና፣ በዕድሜያችን ላይ ተጨማሪ
ቀን ተሰጥቶናልና እስኪ እናመስግን! መከራ ቢበዛም፣ ውጊያ ቢበረታም፣ ጌታ በዙፋኑ ላይ ነው!
ታውቃላችሁ፣ ወዳጅ ቢከዳን፣ ወንድሞች ቢያገልሉን፣ ኑሮ እስር ቢሆን፣ ልባችን አይውደቅ! ስለሆነው
ሁሉ፣ ጌታን እናመስግን! በምስጋና ውስጥ ድል፣ በዝማሬ ክብር አለና፣ እስኪ እናመስግን!
ወዳጄ፣ ኑሮ ከብዶብዎት ከኑሮ አጣብቂኝ ውስጥ ገብተው ተጨንቀው ይሆናል! ግድ የለዎትም፣ ከመከራ
አጣብቂኝ ገብተው ተጨንቀው ይሆናል! እስኪ ያመስግኑ! የሚያመልኩት ጌታ ሰምቶ የሚመልስ፣ አይቶ የሚራራ አምላክ ነውና፣ እስኪ ያመስግኑ!
በምስጋና ውስጥ ድል፣ በዝማሬ ውስጥ ክብር አለና፣ ጌታንያመስግኑ!
-------------------------
(ይህን
ዕለታዊ
ዲቮሽን
ላይክና ሼር ያድርጉ፣ ወዳጅ ጓደኞችዎም
እንዲያገኙ
ያግዙ፡፡
ይህን አገልግሎት ለመደገፍና የእምነት ዘራችሁን ለመዝራት (Tesfahun Hatia
Daka, Commercial Bank of Ethiopia, Andinet Branch; A/C 1000036318949; Swift Code: CBETETAA) መላክ ትችላላችሁ፡፡ ለዘሪ ዘርን የሚሰጥ ጌታ ዘራችሁን ይባርክልኝ!)
No comments:
Post a Comment