Saturday, October 18, 2014

የሬሳ ቤት መስተዋቶች!

ዲቮሽን ቁ.38/07     ቅዳሜ፣ ጥቅምት 8/07 ዓ.ም.  
(በመጋቢ ተስፋሁን ሐጢያ)


 የሬሳ ቤት መስተዋቶች!


ጩኽ የሚል ሰው ቃል ምን ብዬ ልጩኽ? አልሁ። ሥጋ ለባሽ ሁሉ ሣር ነው፥ ክብሩም ሁሉ እንደ ምድረ በዳ አበባ ነው። (ኢሳ 40፡6-8)

የሰው ልጅ በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴው፣ ራሱን ለመመልከት የሚችልባቸው ሶስት ዓይነት መስተዋቶች አሉ፡፡ እነርሱም የቤት፣ የውጭና የሬሳ ቤት መስተዋቶች ናቸው፡፡

የቤት መስተዋቶች የሚገኙት በየመኖሪያ ቤቱ ግድግዳ፣ ቁምሳጥን፣ ድሬሲንግ ቴብል ለይ ነው፡፡ እነዚህ መስተዋቶች ውጫዊ መልካችንን፣ የላይ-ላይ ገጽታችንን… የሚያመለክቱ ሲሆኑ፣ ለጭቂት ጊዜ ታይተው የሚረሱ ቅርጾቻችንን የሚያሳዩን ናቸው፡፡

የውጭ መስተዋቶች የሚገኙት ከቤታችን ውጭ ባሉ አካባቢዎች ነው፡፡ ከቤት ውጭ የምናደርገው እንቅስቃሴ፣ የመንሠራው ሥራ፣ የሚኖሩንን ማናቸውንም ዓይነት ግንኙነቶች፣ ውስጥ የምናገኛቸው ሕያዋን የሆኑ የሰው ልጆች ናቸው፡፡ እነዚህ መስተዋቶች ባህርያችንን አይተው፣ ምግባራችንን አመዛዝነው… ማንነታችንን በድንግዝግዝ ይነግሩናል፡፡

የሬሳ ቤት መስተዋቶች የሚገኙት ደግሞ የሞቱ ሰዎች በጊዜያዊነት በሚቆዩባቸው መኖሪያ ቤቶች፣ ሆስፒታሎች፣ ጤና ጣቢያዎች…ነው፡፡ እነዚህ መስተዋቶች፣ ትክክለኛውን ማነነታችንን ከሕሊና በማይጠፋ መልኩ የሚመሰክሩ፣ እውነተኛውን ቅርጻችንን የሚጠቁሙና ውስጣዊ እኛነታችንን … በብሩህ ሁኔታ የሚነግሩን ናቸው፡፡

ብዙ ሰዎች በትምህርት ደረጃቸው፣ በሀብታቸው፣ በውበታቸው … በመታበይ ‹‹ዓለም በጥፍሬ›› እያሉ ይመጻደቃሉ፡፡ አንዳንዶች ደግሞ ራሳቸውን ሰው ከማይደርስበት ሩቅ ዓለም ውስጥ በማስቀመጥ፣ በዚህ ምድር ውስጥ ያለውን ማንኛውንም ዓይነት ነገር በማናናቅ ያጣጥላሉ፡፡ ይኼ የሚሆነው ግን የሬሳ ቤቶችን እስከሚጎበኙ ድረስ ነው!

እጅግ በጣም ብዙ ሰዎች ለሰውነታቸው እጅግ በጣም ብዙ ይጨነቁለታል! ከዚህም የተነሳ በየጊዜው የሚፈበረኩ አዳዲስ ፋሽኖችን አጥብቀው በመከታተል፣ ሰውነታቸውን በእነዚያ ውድ አልባሳትና ጌጣጌጦች ለመሸላለም፣ ለማጊያጊያጥና ለማዳመቅ ቆመው እያለሙ፣ ሳይተኙ ያድራሉ፡፡

የእነዚህ ሰዎች የፋሽን ጥም ለመቁረጥ እንዲቻልም፣ በውጭ ዓለም ያሉ ባለሀብቶች ለአልባሳት ዲዛይነሮች፣ ለሞዴልስቶችና ለጨርቃ ጨርቅ ሰፊዎች በሚሊዮን የሚቆጠር መዋዕለ ንዋይ እያፈሰሱ በቢሊዮኖች የሚቆጠር ገቢ ያፍሳሉ!

ለሰውነታቸው ብዙ የሚጨነቁ ሰዎች ዘመን አመጣሽ አልባሳትን በውድ ዋጋ በመግዛት፣ ለመንበሽበሽ፣ ለመምነሽነሽ፣ ለመሽቀርቀር፡ ለመንቀባረር፣ ለመቆናጠር፣ የፋሽን አምሮት ውሃ ለመጠጣት ከሰው መካከል ጎልተው ለመታየት መሰላላቸውን ለመውጣትና … እግረ መንገዳቸውንም ‹‹ከታችኛው ኅብረተሰብ›› መካከል ለመለየት ይፈልጋሉ፡፡ የሬሳ ቤት መስተዋቶችን እስከሚጎበኙ ድረስ!!!

አንዳንድ ሰዎች ራሳቸውን በአካባቢያቸው ካሉ ሰዎች ጋር በማወዳደርና በማነጻጸር ‹‹እኔ ለምን ከሰው በታች ሆንኩ? ለምን እንደ እከሌ ፋሽን መለዋወጥ አቃተኝ?›› በማለት ይጨነቃሉ፡፡ አንዳንዶች እንዲያውም ከጭንቀታቸው ብዛት ይታመማሉ፡፡

ነገር ግን፣ እነዚህ ሰዎች ወደ ሬሳ ቤት ቢገቡ ማንነታቸውን ፍንትው አድርገው የሚያሳዩ መስተዋቶችን ያገኛሉ፡፡ በእነዚህ መስተዋቶች በመታገዝም ለራሳቸው የሰጡትን የተሳሳተ ምስል ማስተካከል ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ ፣ በሕይወት ያሉ ሰዎች ለፋሽን ይጨነቃሉ፡፡ በሬሳ ቤት ውስጥ ያሉ የሰዎ አስከሬኖች ግን ለፋሽን ደንታ የላቸውም፡፡ ስለሆነም ሁላቸውም ከላይ እስከታች አንድ ዓይነት ዩኒፎርም ይለብሳሉ – ነጭ አቡጀዲ፣ በቃ!

ለዚህም ሳይሆን አይቀርም፣ አንድ አዝማሪ አጭር ቁምጣ ታጥቆ፣ ራሱ ላይ የባላገር በርኖስ አጥልቆ፣ ከጀርባው ላይ አጎዛ ጣል አድርጎ፣ ከእግሩ ሸበጥ አስሮ፣ ‹‹አፈር ለሚበላው ለሚበሰብሰው፣ ለዚህ ፈራሽ ገላ ቁምጣ መች አነሰው›› በማለት የሚያንጎራጉረው፡፡ እውነቱን ነው!

ብዙ ሰዎች የሚተኙበት አልጋ፣ የሚቀመጡበት ወንበር፣ የሚንጠራሩበት ቦታ አይበቃቸውም፣ አይመቻቸውምም! ከዚህም የተነሳ ባለ ሜትር አልጋቸውን ወደ ሜትር ከሀያ፣ ሜትር ከሀምሳ፣ ሁለት ሜትር እያደረጉ፣ የመኝታቸውን ድንበር በመለጠጥ ያሰፉታል፡፡ በዚያውም ላይ ከፍራሽ ፍራሽ፣ ከአንሶላው፣ ከብርድ ልብስ፣ ከአልጋ ልብስ፣ ከትራስ … እያማረጡ ይጠቀማሉ፡፡

በሬሳ ቤት ያሉ አስከሬኖች ግን አልጋ፣ ሶፋ … አያማርጡም፡፡ በተዘጋጀላቸው ጠባብ ሳጥን ውስጥ ሰተት ብለው ገብተው፣ ጠበበኝ፣ በረደኝ፣ ጎረበጠኝ፣ ቆረቆረኝ፣ ኮሰኮሰኝ … ሳይሉ ለጥ ሰጥ፣ ጸጥ ረጭ ብለው መተኛት ብቻ ነው!

አንዳንድ ሰዎች አልጋቸውን በዚያ ሁሉ የቅንጦት ዕቃ ቢያሟሉም፣ አርፈው እንቅልፋቸውን መተኛት ያቅታቸዋል፡፡ ለምሳሌ፣ ከተኙበት አልጋ ወዲያ ወዲህ እየተገላበጡና እያንኮራፉ የሚያሰሙት ጩኸት ለሌላው ተኝታ አዋኪ ነው፡፡ በሬሳ ቤት ያሉ አስከሬኖች ግን ከዚህ ችግር ነጻ ናቸው፡፡ ከተመደበላቸው ቦታ ሳይነቃነቁ፣ ከተሰጣቸው ድንበር ሳያልፉ፣ ሳይገላበጡና ሳያንኮራፉ በመጋደም፣ በጋራ ዶርም ውስጥ ካሉ ሌሎች ባልደረቦቻቸው ጋር ተኝተው የማይረበሽ እንቅልፋቸውን ይለጥጣሉ፡፡

ሰዎች ውድ የሆኑ ጌጣጌጦችን በመግዛት፣ ሰውነታቸውን ለመሸላለም ይጨነቃሉ፡፡ ለምሳሌ፣ በእጃቸው አንጓ ላይ ማሠሪያቸው ከወርቅ የተሠሩ ዘመናዊ ሰዓቶችን፣ የወርቅ ካቴናዎችን ያገለድማሉ!  በጣቶቻቸው ላይ በቄንጠኛ ዲዛይነሮች የተሸመኑ እጅግ ውድ የወርቅ የዲያመንድ ቀለበቶች ያጠልቃሉ፡፡ ለአንገታቸው ዝርግፍ ሀብል፣ ለጆሯቸው ዝልዝል ጉትቻ፣ ለእግራቸው ጥምጥም አልቦ … ያደርጋሉ፡፡

በሬሳ ቤት ለሚገኙ የአስከሬን ማኅበረሰብ አባላት እነዚህ ጌጣጌጮች፣ ፈርጣ ፈርጮችና ምርጣ ምርጦች ሁሉ ኩሽ ማንኩሽ ናቸው፡፡ ሌሎች ተመኝተው፣ ተመቀኝተው፣ ተበድረውም ሆነ ተለቅተው ሊያገኟቸው የሚፈልጓቸውን እነዚህን ውድ ኝቃዎች፣ እነርሱ ሒሳብ አውጥተው፣ ዋጋ ከፍለው አይሸምቷቸውም! እንዲያውም በአጠገባቸው እንደ ዝናብና በረዶ ቢዘንቡ እንኳ፣ አንዳቸውንም ንክች አያደርጓቸውም!

የሰውን ልጅ የሚያስጨንቋቸው ነገሮች ‹‹ምን እንበላለን? ምን እንጠጣለን? ምን እንለብሳለን?›› … የሚሉ አንገብጋቢ ጥያቄዎች ናቸው፡፡ ሆኖም ‹‹ሕይወት ከምግብ፣ ሰውነትም ከልብስ እንደሚበልጥ›› ይዘነጋሉ፡፡

በመሆኑም፣ ባለን የትምህርት ደረጃ፣ ሀብት፣ ዝና፣ ውበት…ከሌሎች የምንበልጥ መስሎ ለሚሰማን ሰዎች፣ ከላይ የቀረቡት ዝርዝር ጉዳዮች ግንዛቤ ሰጥተውናል ብዬ አምናለሁ፡፡ የሬሳ ቤት መስተዋቶች እንደሚያሳዩን፣ ሰውነታችን አፈር መሆኑን፣ አንድ ቀንም ወደ አፈር እንደሚመለስ በማወቅ፣ ሰውነታችንን ከሚገባው በላይ ለማቀናጣት በማሰብ ያን ያህል እንዳንጨነቅ ያሳስቡናል!
---------------------------
ማስታወቂያ፣

(1) ጌታ ቢፈቅድ፣ ከመስከረም 1 እስከ ሕዳር 30/07 ያለው ዕለታዊ ዲቮሽን በመጽሐፍ ታትሞ ኢንተርኔት ለማይጠቀሙ ሐበሾች የማድረስ ራዕይ አለኝ፡፡ ስለሆነም፣ ይህን ራዕይ በገንዘብ በመደገፍ አገልግሎቱን ለማሳደግ ልባችሁ የተነሳሳ ወገኖች አነሰ በዛ ሳትሉ የእምነት ዘር በመዝራት ከጎኔ እንድትቆሙ በጌታ ፍቅር እጠይቃለሁ፡፡ የፍቅር ስጦታችሁን (Tesfahun Hatia Daka, Commercial Bank of Ethiopia, Andinet Branch; A/C 1000036318949Swift Code: CBETETAA) በማለት መላክ ትችላላችሁ፡፡ ለዘሪ ዘርን የሚሰጥ ጌታ ዘራችሁን ይባርክ!
(2) ጌታ ቢፈቅድ ከአዲሱ የፈረንጆች ዓመት 2015 ጀምሮ፣ ከአማርኛው ዕለታዊ ዲቮሽን በተጨማሪ፣ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ዕለታዊ ዲቮሽን እጀምራለሁ፡፡ ይህ አገልግሎት በመላው ዓለም የሚገኙ የእንግሊዝኛ ቋንቋ የሚግባቡትን ሁሉ ለመድረስ ኢላማ ያደረገ ነው፡፡ ስለሆነም፣ በጸሎታችሁ እንድታስቡኝ በጌታ ፍቅር አደራ እላለሁ፡፡


(3) ‹‹የወንጌላዊው እጮኛ›› በሚል ርዕስ የተዘጋጀና በወንጌል አገልጋዮች ላይ የሚያጋጥሙ እውነተኛ ልብ አንጠልጣይ ታሪኮችን አሰባስቦ የያዘ መጽሐፍ ጌታ ቢፈቅድ በዚህ ወር መጨረሻ ላይ ለንባብ ይበቃል፡፡ ይህን መጽሐፍ በመግዛት ዕለታዊ ዲቮሽኑን እንድትደግፉ በአክብሮት እየጠየቅሁ፡፡ በአገር ውስጥ ያላችሁም ሆነ ከአገር ውጭ መጽሐፉን በመን መንገድ ልልክላችሁ እንደምችልም መረጃ እንድትሰጡኝ በአክብሮት አሳስባለሁ፡፡ የመጽሐፉ መሸጫ ዋጋ በሚቀጥለው ሳምንት ይፋ ይሆናል! ጌታ ይባርካችሁ! 

No comments:

Post a Comment