Tuesday, October 7, 2014

ያልተገላበጠ ቂጣ !



ዲቮሽን ቁ.27/07     ማክሰኞ፣ መስከረም 27/07 ዓ.ም.
(በመጋቢ ተስፋሁን ሐጢያ)



ያልተገላበጠ ቂጣ   !



ኤፍሬም ከአሕዛብ ጋር ተደባለቀ ኤፍሬም እንዳልተገላበጠ ቂጣ ነው። እንግዶች ጕልበቱን በሉት፥ እርሱም አላወቀም ሽበትም ወጣበት፥ እርሱም አላወቀም። የእስራኤልም ትዕቢቱ በፊቱ መሰከረ ወደ አምላካቸው ወደ እግዚአብሔር ግን አልተመለሱም፥ በዚህም ሁሉ አልፈለጉትም። (ሆሴ 7፡7-10)



ከአስራ አምስት ዓመት በፊት በሕልሜ ያየሁትን ነገር ባስታወስኩ ቁጥር ሁሌ ያቅለሸልሸኛል፡፡ አሁን ይህን ጽሁፍ የምጽፈው በጣም እየቀፈፈኝና እያቅለሸለሸኝ ነው፡፡

ጦጣ ለምሳ ጋብዛኝ ወደ ቤቷ ሄጄ ነበር፡፡ ወደ ቤቷ ደርሼ፣ አንገቴን ከቤቱ ገና እንዳስገባሁ የተቀበለኝ እጅግ ዘግናኝ የሆነ ጠረን ነው፡፡ ከጠረኑ አስቀያሚነት የተነሳ ወደላይ ወደላይ ሊለኝ ታገለኝ፡፡ የቤቷ ሁኔታ ለዓይንም ለአፍንጫም ፈጽሞ የማይመች ቀፋፊ ነው፡፡ ትኩስና አስቀያሚ ጠረን ያለው የጦጣዋ አይነምድር እዚህም እዚያም ተጥሎ ይታያል፡፡ የጦጣዋ ኩስ ያልተበተነበት ለመቀመጫ የሚሆን ደህና ቦታ የለም፡፡ ሲጀመር ቤቱ እንኳን ሊቀመጡት ሳይቅለሸለሹ ለሰከንዶች ያህል እንኳ ታግሰው ሊመለከቱት አይችሉም፡፡

እኔ ግን ይህ ሁሉ ሳለ፣ በይሉኝታ ተጠፍንጌ፣ ጦጢት በኩሶቹ መካከል የሆነ ጠባብ ደረቅ ቦታ ላይ ያለ ኩርንችት ጉቶ አሳየችኝና ተሸማቅቄ ተቀመጥሁ፡፡ በአንድ እጇ አስቀያሚ ሙቀጫ ላይ ቡና እየወቀጠች፣ በሌላው እጇ ቆሎ ነገር ትበላ ነበር፡፡ የተቀመጨችበት በኩስ የተጨማለቀ ቦታ ላይ ነው፡፡ ሐፍረተ ሥጋዋ አልተሸፈነም፡፡ አበላሏ፣ አኳኋኗ ሁሉ ነገሯ ሲበዛ ያስጠላል፡፡ ነገር ግን፣ ተጋብዤ የሄድኩት ለምሳ ነውና፣ እየቀፈፈኝ ውስጤን ተረብሾ፣ ወደላይ ወደላይ ሊለኝ እየለበቀኝ በይሉኝታ ተይዤ ቁጭ ብዬ ምግቡን በመጠባበቅ ላይ ሳለሁ በድንገት ነቃሁ፡፡

ያየሁት ሕልም የእውነት ያህል ስሜት በውስጤ ፈጥሮ ስለነበር የእውነትም ወደላይ ወደላይ ይለኝ ጀመር፡፡ የጦጢት ቤት ክርፋቱ በአፍንጫዬ ይሸትተኝ ነበር፡፡ መላ ሰውነቴም በሕልሙ ያየሁትን ኩስ ኩስ ይሸትት ነበር፡፡ መንፈሴ በጣም ታወከ፡፡ ኪራይ ለኪራይ እንከራተት በነበሩት በእነዚያ ዓመታት፣ ተከራይተን የምንገባባቸው ሰፈሮች በየሐይማታዊ ክብረ በዓላት ‹‹ጸበል ቅምሻ›› እንጠራ ነበር፡፡

ተወልጄ ባደግሁበትት በደቡብ አካባቢ ስለሐይማኖታዊ ክብረ በዓላት አጋንንታዊነት ዕውቀቱ ብዙም አልነበረኝም፡፡ ስለሆነም፣ በቃ በየተገኘው ሁሉ ምንም ሳይመስለኝ እሄድ ነበር፡፡ ባለቤቴ ባደገችበት አካባቢ በእነዚህ ክብረበዓላት ውስጥ ያለውን ነገር ጠንቅቃ ስለምታውቀው አጥብቃ ትቃወማለች፡፡ እኔ ግን በይሉኝታም በስንፍናም እየተያዝሁ፣ ‹‹ቅመስ›› እያሉ በሚጠሩኝ ክብረበዓላት እየሄድኩ ከአልኮል መለስ ያለውን ‹‹ቅምሻ››ቸውን ሆዴ እስኪቆዘር ድረስ ጠግቤላቸው እመለሳለሁ፡፡

ሕልሙን አየሁ፡፡ የመንፈስ ዓይኖቼ ተገልጠው የጦጣዋን ‹‹መስ›› አየሁ፡፡ ቤቷን አየሁ፡፡ ምግቧን አየሁ፡፡ ቡናዋን አየሁ፡፡ ጀበናዋን አየሁ፡፡ መቀመጫዋን አየሁ፡፡ ሁሉ ነገሯን አየሁ፡፡ ይህን ካየሁ ወዲህ፣ ‹‹በቅምሻው›› ላይ ማዕቀብ ጥያለሁ፣ ከአሕዛብ አማልክት ዝምድና ትቻለሁ፡፡

ኤፍሬም (የእስራኤል ሕዝብ) ከአሕዛብ ጋር ተደባለቀ፡፡ ከአሕዛብ ጋራ ኮከቡ ገጠመ፡፡ ውሎና አዳሩ አሕዛብኛ ሆነ! ከአንድ ጎኑ ያረረ፣ ከአንድ ጎኑ ጥሬ! ዳቦው ሊጥ ሆነ! የዋርካ ትል ውስጥ ውስጡን ቦርቡሮ በልቶ እንዲጨርስ፣ ጨርሶም እንዲጥል፣ የኤፍሬም ጉልበቱ በእንግዶች ተበላ፣ ተበልቶም አለቀ፡፡ ትል የበላው ዋርካ ሳያውቀው እንዲወድቅ፣ የኤፍሬም ጉልበቱ በነቀዝ ሲበላ፣ ዕድሜና ዘመኑ በአሕዛብ ሲበላ፣ ኤፍሬም አላወቀም፡፡ ውሃ እያሳሳቀ እንዲወስድ፣ አሕዛብ ኤፍሬምን በድግስ በግብዣ ሳያውቀው ወሰዱት! ወስደው ደባለቁት፣ ደባልቀው አቦኩት፣ አቡክተው ጋገሩት፣ ጋግረው አሳረሩት፣ አሳርረው ጣሉት! ይህ ሁሉ ሆኖ ኤፍሬም ወደ እግዚአብሔር አልተመለሰም፡፡

ታውቃላችሁ፣ ከአሕዛብ ጋር ዝምድና ከእግዚአብሔር ያርቃል፡፡ እግዚአብሔርን መውደድ ዓለምን መጥላት ነው፡፡ የአሕዛብ አማልክት አጋንንቶች ናቸው፡፡ ክብረ በዓሎቻችንን የአጋንንት ማህበራት ናቸው፡፡ በየክብረ በዓሎቹ የጭለማ ስራዎች ይሰራሉ፡፡ ስዕለትና ልመና፣ ቅብዐትና ጥንቆላ ይፈጸማሉ፡፡ የእግዚአብሔር ሕዝብ ከአጋንንት ማህበር ጋር አቻና ጋብቻ፣ ዘርና ዝምድና የለውም፡፡ ብርሃን ከጭለማ ጋር፣ የዳኑት ካልዳኑት ጋር የበዓላት ኅብረት ሊኖራቸው አይችልም፡፡

(ይህን ዕለታዊ ዲቮሽን ላይክ እና ሼር ያድርጉ፣ ወዳጅ ጓደኞችዎም እንዲያገኙ ያግዙ፡፡ ዲቮሽኑ ሳይቋረጥ ዓመቱን ሙሉ እንዲቀጥል በጸሎትዎና ጌታ በልብዎ በሚያስቀምጥ ማናቸውም ነገር ሁሉ ይደግፉ፡፡ ጌታ ይባርክዎ፡፡)

1 comment:

  1. ቅምሻ ያልከውማ የእግዚአብሔር ስም ተጠርቶበት ነው። ያስከፋክ ቅምሻው ለምን ጉርሻ አሎነም ብለ ነው። የቀኝ ገዥዎች ሃይማኖት እንደዚህ ያስወራል።

    ReplyDelete