Wednesday, October 8, 2014

አታልቅስ!


ዲቮሽን ቁ.28/07     ረቡዕ፣ መስከረም 28/07 ዓ.ም.
(በመጋቢ ተስፋሁን ሐጢያ)


አታልቅስ!

…መጽሐፉን ሊዘረጋ ወይም ሊመለከተው የሚገባው ማንም ስላልተገኘ እጅግ አለቀስሁ። ከሽማግሌዎቹም አንዱ። አታልቅስ፤ እነሆ፥ ከይሁዳ ነገድ የሆነው አንበሳ እርሱም የዳዊት ሥር መጽሐፉን ይዘረጋ ዘንድ …ማኅተም ይፈታ ዘንድ ድል ነሥቶአል አለኝ። (ራዕይ 5፡4-5)

በሕይወታችን ብዙ ያልተፈቱ እንቆቅልሾች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ በነፍሳችን ውስጥ ብዙ ጥያቄዎች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ በመንፈሳችን ውስጥ ያልፈረሰ ምሽግ፣ ያልተፈታ እሽግ ሊኖር ይችላል፡፡ በኑሮአችን ውስጥ ያልተከፈተ ፖስታ፣ ያልተወረሰ ቦታ አለ፡፡ ያልመነጠርነው ጫካ፣ ያልተሻገርነው መልካ፣ የቀበርነው ምስጢር፣ የደበቅነው ነገር፣ ያፈንነው ገበና፣ የወደቅነው ፈተና ይኖራል፡፡ ቤተሰብ የማያውቀው፣ ወዳጅ የማይረዳው፣ የብቻችን ነገር፣ የግላችን ችግር አለ፡፡

ያልወጣነው ተራራ፣ ያላሸነፍነው መከራ፣ ያልተሻገርነው ገደል፣ ያልረታነው ትግል፣ ያልፈታነው እስር አለ፡፡ ያልተያዘ እርሻ፣ ያልተወረሰ ድርሻ አለ፡፡ ያልተቆፈረ ጉድጓድ፣ ያልተሄደበት መንገድ አለ፡፡ ያልታረሰ መሬት፣ ያልተሰበሰበ ምርት፣ ያልተወሰደ ሀብት አለ፡፡
ተስፋ ቆርጠን፣ አንገት ደፍተን ከሰው ተሸሽገን የምንኖረው ነገር ይኖራል፡ በኑሮአችን ውስጥ የተገለለ ሕይወት፣ ያልተነበበ ድርሰት፣ የተነጠለ ደሴት፣ ያልተመነጠረ ጫካ፣ ያልተቃኘ ዜማ፣ ያልደረስነው ስፍራ፣ ያልረገጥነው ሰፈር፣ ያልገባነው መንደር፣ እሩቅ የሆነ ሀገር አለ፡፡ ከዚህም የተነሳ፣ በነፍሳችን ውስጥ የበረታ ሐዘን፣ ለቅሶ፣ እንባ፣ የእንጉርጉሮ ዜማ ሊኖር ይችላል፡፡ 

ወዳጄ ሆይ፣ አታልቅስ! መከራህንና ችግርህን የይሁዳ አንበሳ ለሆነው ለኢየሱስ ክርስቶስ ተውለት! የከበደንን ሸክም፣ የቸገረንን ነገር ለእርሱ አሳልፈን እንስጠው፡፡ ለጥያቄ መላሽ፣ ለእንቆቅልሽ ፈቺ ነገራችንን እንስጠው፡፡ እርሱ ስለእኛ ያስባልና የሚያስጨንቀንን ሁሉ በእርሱ ላይ እንጣል፡፡ ለእኛ የሚያስባት አሳብ እርሱ ያውቃልና፣ ለእኛ ያለው አሳብ መልካም ነውና፣ ነገራችንን በእርሱ ላይ እንጣለው፡፡

ወዳጄ ሆይ፣ የእንባህ ዋጋ፣ የጸሎትህን ምላሽ አንድ ቀን ተትረፍርፎ ይመለሳልና አይዞህ፡፡ የብቸኝነትን ዓለም የበረታን ሸክም እግዚአብሔር አይቶታል፡፡ ከሰዎች ደብቀሽ የያዝሽውን ምስጢር ኢየሱስ አውቆታል! ለሰው የማታወሪውን እግዚአብሔር ሰምቶታል፡፡ የጉዳትሽን ልክ ክርስቶስ አይቶታል፡፡ በሮችሽን ዘግተሽ፣ ከሰው ተገልለሽ ያፈሰስሽውን እንባ ኢየሱስ አይቶታል! አብሮ እያለቀሰ፣ እንባን እያበሰ መጽናናት ሰጥቶሻል፡፡ ጉዳይሽን ሁሉ ኢየሱስ አውቆታል፡፡ ጸሎትሽን ሁሉ እግዚአብሔር ሰምቶታል፡፡ ስለዚህ፣ በቃ ማልቀስ ይቅር፣ በቃ ማዘን ይቅር – የመፍትሔ ጌታ አለ እግዚአብሔር!

(ይህን ዕለታዊ ዲቮሽን ላይክ እና ሼር ያድርጉ፣ ወዳጅ ጓደኞችዎም እንዲያገኙ ያግዙ፡፡ ዲቮሽኑ ሳይቋረጥ ዓመቱን ሙሉ እንዲቀጥል በጸሎትዎና ጌታ በልብዎ በሚያስቀምጥ ማናቸውም ነገር ሁሉ ይደግፉ፡፡ ጌታ ይባርክዎ፡፡)

No comments:

Post a Comment