ዲቮሽን ቁ.42/07 ረቡዕ፣ ጥቅምት
12/07 ዓ.ም.
(በመጋቢ ተስፋሁን ሐጢያ)
ተከትለው ይሩጡ !
ኤልያስም
አክዓብን፦ የዝናቡ ውሽንፍር እጅግ ነውና ተነሥተህ ውጣ፥ ብላም ጠጣም አለው።…ብላቴናውንም። ወጥተህ ወደ ባሕሩ ተመልከት
አለው። ወጥቶም ተመልክቶም። ምንም የለም አለ። እርሱም፦ ሰባት ጊዜ ተመላለስ አለው። ብላቴናውም ሰባት ጊዜ ተመላለሰ። በሰባተኛውም
ጊዜ። እነሆ፥ የሰው እጅ የምታህል ታናሽ ደመና ከባሕር ወጣች ... የእግዚአብሔርም እጅ በኤልያስ ላይ ነበረች ወገቡንም
አሸንፍጦ ወደ ኢይዝራኤል እስኪገባ ድረስ በአክዓብ ፊት ይሮጥ ነበር (1ነገ 18፡41-46)
ወቅቱ ከባድ የሆነ
የድርቅና የረሀብ ጊዜ ነው! በእስራኤል ምድር ለሶስት ዓመታት ጠልና ዝናብ አልነበረም፡፡ በምድሪቱ ላይ በእህልና ውሃ እጦት ትሰቃይ
ነበር፡፡ ነገር ግን ምግብና ውሃ ብርቅ በነበሩት በእነዚያ ዓመታት እግዚአብሔር ኤልያስን በዮርዳኖስም ትይዩ ባለው በኮራት ፈፋ ውስጥ ሸሽጎት ነበ፡፡
ጠዋትና ማታ እንጀራና ሥጋ በቍራዎች ይመግበው፣ ከወንዝ ውሃም ያጠጣው ነበር፡፡ በዝናብ እጦት ወንዙ ሲደርቅም፣ በሲዶና አጠገብ
ባለችው ሰራፕታ ውስጥ የምትገኝ አንዲት ባልቴት አዝዞለት ትመግበው ነበር፡፡
ከእነዚህ
ዓመታት በኋላ፣ ‹‹በምድር ላይም ዝናብ እሰጣለሁ›› የሚል የእግዚአብሔር ቃል ወደ ኤልያስ መጣ። ይህን ተስፋ ቃል ይዞ ነበር
ኤልያስ ለእስራኤል ንጉሥ ለአክአብ የተገለጠው! በመጣለት ቃል መሠረትም ኤልያስ ከቤቱ ገብቶ ሲጸልይ በመንፈስ እጅግ ብርቱ
የሆነ የዝናብ ውሽንፍር ታየው፡፡
በመንፈስ
የታየውን ነገር በእውን ለማረጋጥም ብላቴናውን ወደ ውጭ ወጥቶ ባሕሩን እንዲመለከት ላከው፡፡ ብላቴናው ምንም የሚታይ ነገር
አለገኘምና ተመልሶ መጥቶ ‹‹ምንም የሚታይ ነገር የለም›› በማለት አስደንጋጭ ሪፖርት አቀረበለት፡፡ ሆኖም የሰማውን
ሰምቶአልና፣ ያየውንም አይቷልና በእግዚአብሔር ላይ ጽኑ እምነት ነበረው! ተስፋ ቃል የሰጠውም የታመነ ነውና በሰማው ሪፖርት ተስፋ
አልቆረጠም!
ብላቴናው
ሰባት ጊዜ እንዲመላለስ አዘዘው! ብላቴናውም ታዝዞ ሪሰርች ማድረጉን ቀጠለ፡፡ ስድስት ዙር ሙሉ እየወጣና እየገባ ‹‹ደመና
የለም፣ ውሽንፍርም አይታይም፣ ምንም ነገር የለም›› እያለ አሰልቺ ሪፖርት ያቀርብ ነበር፡፡ ኤልያስም፣ ‹‹ግዴ የለህም፣ የሰማሁትን
ሰምቻለሁና፣ ያየሁትንም አይቻለሁና መመላላለስህን ቀጥል›› ይለው ነበር፡፡
በሰባተኛው ጊዜ። እነሆ፥ የሰው እጅ የምታህል ታናሽ ደመና ከባሕር
ወጣች፡፡ ወዲያውም ኤልያስ ንጉሡን አክአብንና አብረውት የነበሩትን ሰዎች
ሊወርድ ያለው ከባድ ዝናብ ሳይቀድማቸው በፊት ወደቤታቸው እንዲገቡ አስቸኳይ ትዕዛዝ ሰጠ፡፡ ኤልያስ ደመናውን ተከትሎ ወገቡን አሸንፍጦ ወደ ኢይዝራኤል እስኪገባ ድረስ በአክዓብ ፊት
ይሮጥ ነበር፡፡
ወዳጄ
ሆይ፣ እግዚአብሔርን ያምኑታልን? በቃል እንደተናገረዎ እንደሚፈጸም፣ በራዕይ እንዳሳየዎ እንደሚሆንስ ያምናሉ? የተናገረዎት ሳይፈጸም፣
ያሳየዎትም ሳይሆን እንደማይሞቱስ ያምናሉ? የሚያምኑ ከሆነ፣ እንደዚህ ያድርጉ! ጠላት የሚነግርዎትን ሪፖርት አይስሙ! ጌታ የተናገረዎ
ቃል በእውን ባይታይም፣ ያሳየዎ ራዕይ ቶሎ ባይፈጸምም ተስፋ አይቁረጡ! የሚታይ ነገር በመዘግየቱ፣ ጠላት ማስረጃ አጣቅሶ፣ ማሳመኛ
አላብሶ የሚያቀርብልዎትን ዜና አይቀበሉ! እንደተናገረዎ የሚያደርግ፣ እንዳሳየዎ የሚፈጽም ጌታ እርሱ ታማኝ ነውና በጌታ ይመኑ!
ወዳጄ
ሆይ፣ ጠላት በወጣ በገባ ቁጥር፣ ‹‹የለም፣ የለም›› ሲልዎት አይቀበሉ! በነጋ በጠባ ቁጥር ‹‹የለም፣ የለም›› ሲልዎት
ጆሮዎትን አይስጡ! የሌለውን ነገር ፈጥሮ ወደ መኖር የሚያመጣውን እግዚአብሔርን ይመኑ! ተስፋ የሰጠው የታመነ ነውና
በእግዚአብሔር ይመኑ! ወገብዎትን ታጥቀው፣ ያሳየዎትን ደመና ተከትለው ወደፊት ይሩጡ!
ወዳጄ
ሆይ፣ የሚበላ ቢያጥር፣ የሚጠጣ ቢጎድል፣ የኤልያስ አምላክ መላ አያጣምና አይዞዎት! ለሚታመኑበት ሁሉ እርሱ ታማኝ አምላክ
ነውና ተስፋ አይቁረጡ! ለችግር ላይረቱ ወገብዎትን ይታጠቁ! ያሳየዎትን ደመና ምንም ትንሽ ብትሆን እርሷን ተከትለው ወደፊት ይሩጡ!
የተሰጠዎን ተስፋ ቃል ተከትለው ይሩጡ! የተመለከቱትን ራዕይ ተከትለው ይሩጡ!
-------------------------
(ይህን
ዕለታዊ
ዲቮሽን
ላይክና ሼር ያድርጉ፣ ወዳጅ ጓደኞችዎም
እንዲያገኙ
ያግዙ፡፡
ይህን አገልግሎት ለመደገፍ (Tesfahun Hatia
Daka, Commercial Bank of Ethiopia, Andinet Branch; A/C 1000036318949; Swift Code: CBETETAA) መላክ ትችላላችሁ፡፡ ለዘሪ ዘርን የሚሰጥ ጌታ ዘራችሁን ይባርክልኝ!)
No comments:
Post a Comment