Saturday, October 11, 2014

የልብ ችግር!

ዲቮሽን ቁ.31/07     ቅዳሜ፣ ጥቅምት 1/07 ዓ.ም.  
(በመጋቢ ተስፋሁን ሐጢያ)


የልብ ችግር!  

ለፍጥረታዊ ሰው የእግዚአብሔር መንፈስ ነገር ሞኝነት ነውና አይቀበለውም፤ በመንፈስም የሚመረመር ስለ ሆነ ሊያውቀው አይችልም። … እኛ ግን የክርስቶስ ልብ አለን (1ቆሮ 2፡13-16)።

አንድ ሰውዬ በትንሽ ጀልባ ላይ ሆኖ በመንጠቆ አሳ ያጠምድ ነበር፡፡ ሰውዬው የሚይዘውን እያንዳንዱን ዓሳ በሜትር ይለካ ነበር፡፡ ከሚለካቸው ዓሳዎች መካከል አነስ አነስ ያሉትን ወደ ዕቃው ሲያስገባ፣ ትልልቆቹን ወደ ሐይቁ ይወረውራቸው ነበር፡፡

ሁኔታውን ቆሞ ይታዘብ የነበረ መንገደኛ፣ ዓሳዎቹን ለምን ወደ ሐይቁ እንደሚጥላቸው ጠየቀው፡፡ ሰውዬውም፣ እንዲህ ሲል መለሰለት፡፡ መጥበሻዬ ትንሽ ነው፡፡ የማጠምዳቸውን ዓሳዎች በሜትር የምለካበትም ምክንያቱ ይኼ ነው፡፡ ከመጥበሻዬ መጠን የሚያንሱትን ዓሳዎች እወስዳለሁ፣ የሚተልቁትን እጥላለሁ፡፡

ወገኖች ሆይ፣ በአስተሳሰባችን ምክንያት ስንቱን ጥለን ይሆን! በአመለካከታችን ምክንያት ስንቱን መልካም ነገር አበላሽተን ይሆን? በልብ ጠባብነት ስንቱን ቆንጆ ዕድል አስመልጠን ይሆን?

የአመለካከት ችግር ምንጩ የልብ ችግር ነው! የልብ ችግር የአስተሳሰብ ችግር ያመጣል! የአስተሳሰብ ችግር ብዙ ጉዳቶች ያስከትላል! ብዙ ጊዜ ከአቅማችን በላይ የሆኑ ነገሮችን አንቀበልም፡፡ ከልምዳችን ውጭ የሆኑ ነገሮችን ለመቀበል ስንቸገር ይታያል፡፡ ከባህላችን ውጭ የሆኑ ነገሮችን ለመቀበል ያለን ቁርጠኝነት ደካማ ነው፡፡ ከእውቀታችን ውጭ የሆኑ ነገሮችን እንገፋለን፡፡ ከቤተእምነታችን ውጭ የሆኑ ነገሮችን እንቃወማለን፡፡

ፍጥረታዊ ሰው መንፈሳዊውን ነገር በራሱ መነጽር ይመለከታል፡፡ ለፍጥረታዊ ሰው የእግዚአብሔር መንፈስ ነገር ሞኝነት ነውና ለመቀበል ይቸገራል፡፡ መንፈሳዊ ነገር በመንፈስ የሚመረመር ስለሆነ ሊያውቀው አይችልም። በራሱ መስፈሪያ፣ በራሱ መለኪያ ይገምታልና ሞኝነት ይመስለዋል፡፡ ስለሆነም መንፈሳዊውን ነገር በስጋ እየለካ ይጥለዋል፡፡

ለመንፈሳዊ ሰው የነገሮች መቃኛ፣ መመዘኛ መለኪያ መንፈሳዊ ዓይን ነው! መንፈሳዊውን ነገር በመንፈስ እርዳታ አጥርቶ ያየዋል! ለዓይን ከሚታየውና ለጆሮ ከሚሰማው ይልቅ በመንፈስ ይረዳል! ከሰፈር ኳኳታው፣ ከመንደር ጓጓታው መንፈሱን ይሰማል! የክርስቶስ ልብ ካለው የአይኑ መነጽር ሌንሱ ይቀየራል! 

No comments:

Post a Comment