ዲቮሽን ቁ.30/07
አርብ፣ መስከረም 30/07 ዓ.ም.
(በመጋቢ ተስፋሁን ሐጢያ)
እግዚአብሔርን በማንነቱ ማወቅ!
መስማትንስ በጆሮ በመስማት ሰምቼ ነበር አሁን ግን ዓይኔ አየችህ፤ ስለዚህ
ራሴን እንቃለሁ በአፈርና በአመድ ላይ ተቀምጬ እጸጸታለሁ (ኢዮብ 42፡5-6)።
ዖጻዊው ኢዮብ፣ ቴማናዊው ኤልፋዝ፣ ሹሃዊው በልዳዶስ፣ ነዕማታዊው ሶፋር ከፍተኛ የስነመለኮት ሊቆች (Academic Theologians) ናቸው፡፡ በመጽሐፉ ውስጥ ከተደረጉ ውይይቶች ስንመለከት
የእነዚህ ልሂቃን መሠረተ እምነት (Basic Doctrines) ጤናማ(Sound) ነው፡፡
የቴኦሎጂ ምሁራኖቹ ስለ እግዚአብሔር ያላቸው እውቀት የተከበረ፣ የማስተማር ችሎታቸው የተጨበጨበለት፣ አንደበታቸውም ርቱዕ ነው፡፡ አራቱም
የቴኦሎጂ ምሁራን በየኮሌጆቻቸው ተንተርሰው ስለ እግዚአብሔር ሲከራከሩ፣
ሲጨቃጨቁና ሲቆራቆሱ ሳይግባቡና ሳይተማመኑ ብዙ ጊዜ አጠፉ፡፡
ለካስ ልሂቃኖቹ ከሌሎች ምሁራን ስለ እግዚአብሔር ተማሩ እንጂ፣ ከመጻሕፍት አገላብጠው ስለ እግዚአብሔር አነበቡ
እንጂ እግዚአብሔርን ራሱን በማንነቱ አያውቁትም! ታውቃላችሁ፣ ምሁራኖቹ እንደገደል ማሚቱ የሰሙትንና ያነበቡትን መልሰው ያስተጋቡ
ነበር እንጂ እግዚአብሔርን በማንነቱ አያውቁትም! ስለሆነም እግዚአብሔር ተገልጦ እውቀታቸው ሲፈተሽ ገለባ ነበር – ሕይወት የማይሰጥ፣
ነፍስ የማይመልስ ገለባ!
ታውቃላችሁ፣ ሰው እግዚአብሔርን በማንነቱ ካላወቀው በስተቀር ወደ ሰው ልብ የሚደርስ ቃል አይኖረውም፡፡ ሺህ
ጊዜ ሺህ ቃላት በመደርደር፣ እልፍ ጊዜ እልፍ ስብከት በማሳመር የተሰበረን ልብን መጠገን አይቻልም፡፡ ፊቱን ካላየን በስተቀር የሳተን
መመለስ፣ የወደቀን ማንሳት፣ ያዘነን ማጽናናት አይቻልም፡፡
ታውቃላችሁ፣ የትኛውም መንፈሳዊ ኮሌጅ ይገባ፣ የትኛውም ዲግሪ ይበጠስ፣ የትኛውም ደረጃ ይያዝ እግዚአብሔርን
በማንነቱ የማያሳይ እውቀት ገለባ ነው – ሕይወት የማይሰጥ፣ ሕይወት አልባ ነው! እግዚአብሔርን ለራሱ ያላየ ለሌሎች ማሳየት አይችልም!
ታውቃላችሁ፣ እግዚአብሔርን በመጻሕፍት አንብበን፣ በትምህርት አውቀን አንጨርሰውም! እግዚአብሔር በጥናትና በምርምር
ታውቆ አይጨረስም፡፡ በዲግሪ፣ በማስተርስ፣ በዶክትሬት፣ በስፔሺያላይዝድ ጥናት ታውቆ አይጨረስም!
እግዚአብሔርን ልናውቀው የምንችለው እርሱ ራሱን በገለጠልን መጠን ብቻ ነው! እግዚአብሔር ራሱን የሚገልጠው
ደግሞ ለትሁታንና መንፈሳቸው ለተሰበረ ነው! ስለ እግዚአብሔር ባላቸው እውቀት የሚታበዩ፣ ባደረጉት ምርምር የሚኮሩ፣ በደረሱበት
ደረጃ የሚኮፈሱ፣ ጌታን ከትናንት የተሻለ የማወቅ ዕድል የላቸውም፡፡
ታውቃላችሁ፣ ምድራዊ ዕውቀት ያስታብያል! እርስ በርስ ያጣላል፣ ያከራክራል፣ ያጨቃጭቃል፣ ያናንቃል፣ ጉሮሮ
ለጉሮ ያተናንቃል…ያለ ፍሬም ዕድሜን ይጨርሳል!
ታውቃላችሁ፣ ሰማያዊ ዕውቀት እግዚአብሔርን በማንነቱ ያሳያል! እግዚአብሔር በማንነቱ ያየ ሰው ደግሞ ያውቃል!
የራሱን ማንነት ያወቀ እራሱን ይንቃል፣ ራሱን ዝቅ ያደርጋል! ራሱን ዝቅ የሚያደርግ ደግሞ ከፍ ከፍ ይላል! በጥቂቱ ታምኗልና በብዙ
ይሰጠዋል!
ታውቃላችሁ፣ ሰው መቼም ቢሆን ራስ ወዳድ ነውና፣ ራሱን መናቅ የሚችለው እግዚአብሔርን ያየ እንደሆነ ብቻ ነው!
እግዚአብሔርን ያላየ፣ እራሱንም ያልናቀ ሰው ለሌላው የሚቆረስ ነገር በሕይወቱ የለውም! ስለሆነም፣ በሕይወታችን እግዚአብሔርን ማየት
ይሁንልን! እርሱን ከማየታችን የተነሳም ራስን ማወቅ ይሁንልን!
No comments:
Post a Comment