Sunday, October 12, 2014

ከገብረ ጉንዳን እንማር (#1) ….. ባለው አቅም መሥራት!

ዲቮሽን ቁ.32/07     እሁድ፣ ጥቅምት 2/07 ዓ.ም.  
(በመጋቢ ተስፋሁን ሐጢያ)


ከገብረ ጉንዳን እንማር (#1) ….. ባለው አቅም መሥራት!

ገብረ ጕንዳን ኃይል የሌላቸው ሕዝቦች ናቸው…(ምሳ 30፡25)።

ጉንዳኖች ደቃቅ ፍጥረታት ናቸው! ኃይልም ሆነ የአካል ጥንካሬ የላቸውም፡፡ ነገር ግን ጥበብ አላቸው! ጥበብ ከኃይል ትበልጣለች (መክ 9፡16)፡፡ ከጦር መሳሪያዎች ይልቅ ጥበብ ችሻላለች (መክ 9፡18)፡፡

ጉንዳኖች የአቅማቸውን መጠን ያውቃሉ! የጥበብን ጉልበትም ያውቃሉ! ስለሆነም፣ ጥበብ ተጠቅመው ከአቅማቸው በላይ የሆነ ስራ ይሰራሉ! ለምሳሌ፣ ታላላቅ ዛፎችን በቀላሉ ይገነድሳሉ! ተራራ የሚያካክሉ ኩይሳዎችን ልብ ብለው አይተዋል? በጉንዳኖች የተሠሩ ናቸው፡፡ አቅመ ደካማዎቹ ጉንዳኖች፣ ጥይት የማይበሳቸው (bullet proof) ኩይሳዎች ይሠራሉ!

ታውቃላችሁ፣ ትንሽ ነገር አይናቅም! ትንሽ እሳት ትልቅ ጫካ ያቃጥላል! ትንሽ ስህተት ትልቅ ጉዳት ያመጣል! ትንሽ ጥበብ ትልቅ ውጤት ያስገኛል! ትንሽ ትዕግስት ከትልቅ ስህተት ያድናል! እግዚአብሔርን ከመፍራት ጋር ያለ ጥቂት ነገር ሁከት ካለበት ከብዙ መዝገብ ይሻላል(ምሳ 15፡16)፡፡

ታውቃላችሁ፣ ሙሴ ባህር የከፈለው በትንሽ በትር ነው! ዳዊት ጎልያድን የጣለው በትንሽ ድንጋይ ነው! ጌታችን ኢየሱስ ሕዝብን የመገበው በትንሽ ምግብ ነው!

ወገኖች ሆይ፣ ሰውን በሀብቱ አይተን አንናቅ፣ በመልኩ ምክንያት አንናቅ፣ ሰዉን በቁመት በጾታ አንናቅ፣ በዘር በሀረጉ አንናቅ፣ በቋንቋ በባሕሉ አንናቅ! ከጉንዳኖች እንማር! ከመልክ ከቁመናው፣ ከውበት ከቁንጅናው ምንም የሌላቸው ጉንዳኖች የሚሠሩትን ተአምር ማየት ይገባናል! አቅመ ደካማ፣ አካል ጉዳተኛ እያልን ሰውን አንናቅ! ከአቅመ ደካማ ጉንዳኖች እንማር!

ራሳችንን አንናቅ–ከጉንዳን እንበልጣለንና! አቅማችንን አንናቅ–ጉልበት አለውና! ትንሽ ጊዜን አንናቅ–ትልቅ ስኬት አላትና! ትንሽ ዕድል አንናቅ–ትልቅ ክብር አላትና! ባለን አቅም አንፈር፣ ባለን ነገር አንዘን–ጥበብን ተጠቅመን ባለን አቅም ብንሰራ እንደ ገብረጉንዳኖች ተአምር መፍጠር እንችላለንና! ከገብረጉንዳን እንማር!


(ይህን ዕለታዊ ዲቮሽን ሼር ያድርጉ፣ ወዳጅ ጓደኞችዎም እንዲያገኙ ያግዙ፡፡ ዲቮሽኑ ሳይቋረጥ ዓመቱን ሙሉ እንዲቀጥል በጸሎትዎና ጌታ በልብዎ በሚያስቀምጥ ማናቸውም ነገር ሁሉ ይደግፉ፡፡ ጌታ ይባርክዎ፡፡)

No comments:

Post a Comment