Thursday, October 16, 2014

ወዮልን !

ዲቮሽን ቁ.36/07     ሐሙስ፣ ጥቅምት 6/07 ዓ.ም.  
(በመጋቢ ተስፋሁን ሐጢያ)


ወዮልን !

…ለክርስቶስ ወንጌል እንቅፋት እንዳንሆን ሁሉንም ነገር እንታገሳለን …ወንጌልን የምሰብከው ግዴታዬ ስለሆነ ነው፡፡ ወንጌልን ባልሰብክ ግን ወዮልኝ! (1ቆሮ 9፡12፣16)

ወዳጄ ሆይ፣ በመላው ዓለም ከሚገኙ 16,605 ብሔረሰቦች መካከል 6,958 የዓለም ሕዝቦች ወንጌል እንዳልደረሳቸው ያውቃሉ? በወንጌል አምነው ዳግመኛ ልደት ያገኙ እውነተኛ የክርስቶስ ተከታዮች ቁጥርስ ከዓለም ሕዝቦች መካከል ከ2% በታች መሆኑንስ ያውቁት ይሆን?

ወዳጄ ሆይ፣ በ60 ሀገሮች ወደ 200 ሚሊዮን ክርስቲያኖች በስደት ላይ መሆናቸውን ያውቃሉ? በየ24 ሰዓቱ ውስጥ 480 የክርስቶስ ተከታዮች በእምነታቸው ምክንያት ሰማዕት እንደሚሆኑስ ሰምተው ይሆን? ይህም ማለት፣ በ20ኛው ክፍለዘመን ብቻ የተሰዉት ሰማዕታት ቁጥር ባለፉት 19 ክፍላተዘመናት ውስጥ ከተሰዉት ድምር ስሌት እንደሚበልጥስ ያውቃሉ?

ወዳጄ ሆይ፣ ወንጌል ያልደረሳቸው ሕብረተሰቦች መሃከል 95-97% የሚኖሩት አስር አርባ (10/40) ተብሎ በሚጠራው ክልል መሆኑን ያውቃሉ? ይህ ክልል የሐበሻ ምድር (ኢትዮጵያና ኤርትራ) የሚገኙበት መሆኑንስ ያውቃሉ?

ወዳጄ ሆይ፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኤርትራዊያን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በክርስቶስ ባላቸው እምነት ብቻ በስደት ላይ መሆናቸውን፣ ከነዚህም መካከል ብዙዎች እንደተሰዉ፣ ብዙዎች እጅግ ከባድ ስቃይ መከራ እንደደረሰባቸው፣ ብዙዎች ግፍ እንደተሰራባቸው ያውቃሉ?

ወገኖች ሆይ፣ የሐበሻው ምድር የወንጌልን አደራ የተረከበው ከሐዋርያቱ እጅ ነው! ከሐዋርያቱ እጅ ወዲያው በትኩሱ ወደ ምድራችን የገባውን ይህንን ወንጌል የሚገባንን ያህል አልሠራንበትም! በምድረ ሐበሻው፣ በምድረ አረቡ፣ በምድረ አፍሪካ መስራት እየቻልን የራሳችን ደሴት ሰርተን ተቀመጥን! ለዘመናት ዘመን ስለደሴታችን ቅኔ ስንዘርፍላት፣ ወረብ ስንወርድላት፣ ዘፈን ስንዘፍንላት፣ ታክ ስንጽፍላት፣ ጎፈሬ ሲበጠር፣ ፊሽካ ሲነፋ፣ ዘመናት ተቀጩ!

ታውቃላችሁ፣ ስለወንጌል ደሴት ወሬ ስናወራ፣ ደግሰን ስንጠጣ፣ ጠጥተን ስንሰክር፣ እስክስታ ስንመታ፣ ‹‹ኧረ ጎራው›› ስንል፣ ስንፎክር ስንሸልል፣ ዘመናት ተቀጩ! ከፉከራው ዓለም ከስካር ስንነቃ፣ ደሴቲቱም የለች፣ ዘፈኗም ጠፍታለች!

ታውቃላችሁ፣ አባቶቻችን ወንጌል ላልደረሳቸው ሕዝቦች ከማድረስ ይልቅ፣ ‹‹በአንድ የመርፌ ጫፍ ላይ ስንት መላዕክት ይደንሳሉ›› እያሉ ሲከራከሩና ሲጨቃጨቁ ሲዋጉና ሲገዳደሉ በዘመኑ ያገኙትን ሰፊ የወንጌል ዕድል አበላሽተዋል!

ወገኖች ሆይ፣ ላለፈ ክረምት ቤት አይሠራምና፣ ያለፉ አባቶችን መውቀሱ ምንም አይጠቅመንም! አሁን ተራው የእኛ ነው! ዋናው ጥያቄ መሆን ያለበት፣ በዛሬው ዘመን የምንገኝ እኛስ በትውልዳችን ላይ ምን እየሠራን ነው? ብሎ መጠየቁ የተሻለ ነው! በወንጌል ምስክርነት ስራ ላይ ምን እያደረግን ነው? እንዴት እየወጣን፣ እየገባን ነው?

ምዕመናን በየዕለት ኑሮአቸው፣ በሥራ ትጋታቸው፣ በስነምግባራቸው፣  መልካም ምሳሌ በመሆን ወንጌል ሰባኪዎች መሆን ይችላሉ፡፡ በሰዎች መካከል የፍቅር የሰላም ተምሳሌት በመሆን፣ የእውነትና ጽድቅ ምሳሌ በመሆን፣ ወንጌል መስበክ እንችላለን! በመጸለይ፣ ድሆችን በመርዳት፣ ለወንጌል ሥርጭት ሥራ ገንዘብን በመስጠት፣ ወንጌል መስበክ ይቻላል! ይህ ለያንዳንዳችን የተሰጠ አደራ ነው! ይህን አደራ ባንወጣ ግን ወዮልን!

ታውቃላችሁ፣ በብዛቱ ከ6.7-7 ቢሊዮን የሚገመት የዓለም ሕዝብ በየ5 ቀኑ 1.2 ሚሊዮን ያድጋል፡፡ ወንጌልን ካልሰማ ይህ ሁሉ ሕዝብ ወደ ሲኦል ይወርዳል፡፡

ወንጌልን ባለመስበካችን የብዙ ሚሊዮኖች ነፍስ ወደ ሲኦል እየገባች ነው! ለዚህም መጠየቃችን አይቀርም! ያለፈው አልፏልና፣ አሁን እንንቃ! አፋችንን ከፍተን ስለኢየሱስ እንናገር! በቃል በምግባራችን፣ በስራ በኑሮአችን በመልካም ምሳሌ እየተመላለስን ኢየሱስን እናሳይ! በምንኖረው መንደር፣ በምንሠራው መሥሪያ ቤት፣ በምናደርገው ጌጣጌጥ፣ በምንገዛው አልባሳት፣ በማናቸውም ነገር በተገኘው ዕድል፣ ወንጌልን እንስበክ! ለሌሎች መሰናክል አንሁን! በኑሮአችን ሁሉ ሰዎች እኛን አይተው ጌታን እንዲያገኙ ምሳሌ እንሁን! 
---------------------------

(ይህን ዕለታዊ ዲቮሽን ላይክና ሼር ያድርጉ፣ ወዳጅ ጓደኞችዎም እንዲያገኙ ያግዙ፡፡ ዲቮሽኑ ሳይቋረጥ ዓመቱን ሙሉ እንዲቀጥል በጸሎትዎና ጌታ በልብዎ በሚያስቀምጥ ማናቸውም ነገር ሁሉ ይደግፉ፡፡ ጌታ ይባርክዎ፡፡)

No comments:

Post a Comment