Wednesday, October 15, 2014

ከገብረ ጉንዳን እንማር (#4) ….. የተግባቦት ዘዴ!

ዲቮሽን ቁ.35/07     ረቡዕ፣ ጥቅምት 5/07 ዓ.ም.  
(በመጋቢ ተስፋሁን ሐጢያ)


ከገብረ ጉንዳን እንማር (#4) ….. የተግባቦት ዘዴ!

አንተ ታካች፥ ወደ ገብረ ጕንዳን ሂድ፥ መንገድዋንም ተመልክተህ ጠቢብ ሁን። አለቃና አዛዥ ገዢም ሳይኖራት መብልዋን በበጋ ታሰናዳለች፥ መኖዋንም በመከር ትሰበስባለች።…(ምሳ 6፡6-8)።

ጉንዳኖች ያለ አለቃ፣ ያለ አዛዥ፣ ያለ ተቆጣጣሪ በሥራቸው ውጤታማ መሆን ከቻሉበት ምክንያቶች አንዱ የተግባበቦት ዘዴያቸው ነው፡፡ ጉንዳኖች ከፍተኛ የተግባቦት ችሎታ አላቸው፡፡ ጉንዳኖች የሚሄዱት ባንድ መስመር ላይ ነው፡፡ እህል ፍለጋ የሚሄደውም ሆነ እህል ተሸክሞ የሚመለሰው የሚጠቀሙት አንድ መንገድ ነው፡፡

የግጭት አፈታት ምሁራን ሲናገሩ በሰዎች መካከል ግጭት እንዳይፈጠር ከተፈለገ ሰዎች በተለያየ መስመር ላይ ቢጠቀሙ የተሻለ እንደሆነ ይመክራሉ፡፡ ሰዎች በአንድ መስመር ላይ አብረው ሲሰሩ ግጭቶች ይከሰታሉ፡፡ በተለይም የላይላይና ታይታይ የሥራ ግንኙነት በአንድ መስመር የሚገናኝ ከሆነ ግጭቱ ከፍ ያለ ይሆናል፡፡ ግንኙነቱ ከአንድ አቅጣጫ ወደ ሌላ አንድ አቅጣጫ ብቻ ከሆነ መካከለኛ ነው በማለት ያስተምራሉ፡፡ በገብረጉንዳኖቹ የስራ ግንኙነት አንጻር ይህ ፍልስፍና ሲፈተሽ ውድቅ ነው!

ገብረጉንዳኖችየሚሰሩት በአንድ መስመር ላይ ሲሆን፣ የላይላይና ታይታይ መንገዳቸው አንድ ነው! ሆኖም በጎዳናቸው ላይ አይጋጩም፣ አይጣሉም፣ አይጋፉም፣ አይጎሻሸሙም!  

ታውቃላችሁ፣ ገብረጉንዳኖች በመንገዳቸው ላይ የማይገፈታተሩት መስመራቸውን ጠብቀው ስለሚሄዱ ነው! ይህም ብቻ አይደለም! በመስመራቸውም ላይ ሲገናኙ  አንቴና በመነካካት መረጃ ይለዋወጣሉ፡፡ ይህም ብቻ አይደለምአንዳቸው ለሌላቸው ቅድሚያ ይሰጣሉ!

ታውቃላችሁ፣ ሰው ሁሉ ቢግባባ፣ ቢማማር፣ ቢረዳዳ፣ ቢደጋገፍ፣ አንዱ ያለውን ለሌላው ቢያካፍል፣ አንዱ ያየውን ለሌላው ቢያሳይ ሁሉም ውጤታማ ይሆናል! በተለይም በክርስቶስ አምነን ዳግመኛ የዳንን ምዕመናን እንደ ገብረጉንዳኖች መሆን ይጠበቅብናል፡፡ በምድር ስንመላለስ በቃሉ መሠረት መኖር ግድ ይለናል፡፡

ታውቃላችሁ፣ በሀገራችን ለዘመናት ሥር ሰድዶ የቆየው የብሔረሰቦች አለመተማመንና በሰላም ጊዜ አብሮ መሥራት አለመቻል ጎድቶናል! እንደ አንድ ሀገር ዜጎች ለአንዲት አገር ዕድገት ለአንድ አገር ሕዝብ ባንድ ባንዲራ ሥር መቆም አቅቶናል! የቋንቋ የብሔር የክልል መስመሮች ከፋፍለው አንቀውናል!

ወገኖች ሆይ፣ የዓለም ፖለቲካ፣ የዓለም ፍልስፍና፣ የዓለም ጎዳና ለምዕመናን አንድነት፣ ለኃጢአታችን ሥርየት፣ ለሥጋ ትንሣኤ፣ ለዘላለም ሕይወት ጥቅም አይሰጠንም! ቋንቋ ብሔራችን ባሕል ክልላችን ታሪክ ሁኔታችን ፍቅርን አልሰጡንም! አብረን እንድንሠራ፣ አብረን እንድንቆም ሊያደርጉን አልቻሉም! ለዘመናት የኖርነው እርስ በርስ ስንናቆርና ስንደናቆር ነው! በደሙ የገዛን፣ ከነገድ፣ ከቋንቋ፣ ከወገን፣ ከሕዝብም ዋጅቶ ለአምላካችን መንግሥትና ካህናት ያደረገን ኢየሱስ ብቻ ነው! የተለያየን ቋንቋ የሚያግባባ ጌታ፣ የተለያየ ብሔር የሚያስማማ አምላክ፣ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ብቻ ነው! ከሞተ ሰውነታችን፣ ካረጀ ብሔራችን ወጅቶ የራሱ ያደረገን ኢየሱስ ብቻ ነው! የተግባቦታችን ምስጢር የርሱ መሆናችን ነው!

ወገኖኖች ሆይ፣ ከጉንዳን እንማር! እንደ ገብረ ጉንዳኖች ያለ ክልል ገደብ፣ ያለ ብሔረሰብ፣ ያለ ፖለቲካ፣ ያለ ቋንቋ ምርጫ፣ በክርስቶስ ብቻ በአንድ መስመር ገብተን አብረን መሄድ እንችላለን!

ታውቃላችሁ፣ ያለ ደጋፊ፣ ያለ ተቃዋሚ፣ ያለ አኩራፊ ፓርቲ በክርስቶስ መስመር እንመላለሳለን! በዚህ መስመር ሳለን፣ በክርስቶስ ያገኘነውን አንድነታችንን የሚበታትነውን፣ መንፈሳዊ ቋንቋ የሚደባልቀውን፣ የፍቅራችንን ዜማ የሚያበላሸውን፣ የበራልንን ብርሃን የሚያጨልመውን፣ የምዕመናንን ሰላም የሚያደፈርሰውን፣ የሰማይ ዜግነታችንን ምድራዊ የሚያደርገውን ምሽግን እንሰብራለን፣ በእግዚአብሔር እውቀት ላይ የሚነሣውን ከፍ ያለውን ነገር ሁሉ እናፈርሳለን! (ተፈጸመ)


---------------------------

(ይህን ዕለታዊ ዲቮሽን ላይክና ሼር ያድርጉ፣ ወዳጅ ጓደኞችዎም እንዲያገኙ ያግዙ፡፡ ዲቮሽኑ ሳይቋረጥ ዓመቱን ሙሉ እንዲቀጥል በጸሎትዎና ጌታ በልብዎ በሚያስቀምጥ ማናቸውም ነገር ሁሉ ይደግፉ፡፡ ጌታ ይባርክዎ፡፡)

No comments:

Post a Comment