Tuesday, October 14, 2014

ከገብረ ጉንዳን እንማር (#3) ….. ጊዜውን ማወቅ!

ዲቮሽን ቁ.34/07     ማክሰኞ፣ ጥቅምት 4/07 ዓ.ም.  
(በመጋቢ ተስፋሁን ሐጢያ)


ከገብረ ጉንዳን እንማር (#3) ….. ጊዜውን ማወቅ!

አንተ ታካች፥ ወደ ገብረ ጕንዳን ሂድ፥ መንገድዋንም ተመልክተህ ጠቢብ ሁን። አለቃና አዛዥ ገዢም ሳይኖራት መብልዋን በበጋ ታሰናዳለች፥ መኖዋንም በመከር ትሰበስባለች።…(ምሳ 6፡6-8)።

ጉንዳኖች ጊዜን ያውቃሉ፡፡ እህል የሚገኝበትን ጊዜ፣ የማይገኝበትንም ወቅት ያውቃሉ፡፡ ስለሆነም እህል በሚገኝበት በበጋው ጊዜ መኖአቸውን ይሰበስባሉ፡፡ በበጋው ጊዜ የሰበሰቡትን ምግብ፣ እህል ለማይገኝበት ለክረምቱ ጊዜ ያስቀምጣሉ፡፡ በበጋው ጊዜ እህል አገኘን ብለው አይዘናጉም! ከእህሉ እርሻ ያገኙትን በልተው፣ የበሉትን ጠግበው፣ የጠገቡትን ደፍተው አይሄዱም፡፡

ጉንዳኖች፣ ለዛሬ የሚሆናቸውን ይበሉ ይጠጡና ለነገው የክረምቱ ጊዜ የሚሆናቸውን ደግሞ ወደ ቤታቸው ይዘው በመሄድ በመጋዚናቸው ያስቀምጣሉ፡፡ በዚህ መልኩ አስቀድመው ተዘጋጅተዋልና፣ ክረምቱ ሲመጣ አይፈሩም፡፡ እህል ተወደደ፣ ገበያው ነደደ ብለው አይሰጉም! እንደ ባለራዕይ መጭውን ጊዜ አስቀድመው አውቀው ተገቢውን ስራ በተገቢው ጊዘዜ ሰርተዋልና ፍርሃት አይዛቸውም!

ወገኖች ሆይ፣ ነገ በእኛ እጅ አይደለም፡፡ ነገ ያለው በእግዚአብሔር እጅ ነው፡፡ እንደ መንፈሳዊ ሰው ስለ ነገ መፍራትና መጨነቅ የማይገባ ቢሆንም እንደ ባለራዕይ የወደፊቱን ሁኔታ አስቀድሞ ማሰብ ተገቢ ነው፡፡ ነገን ላለመጨነቅ የዛሬውን ጊዜ በሚገባ መኖር ነው፡፡ ከነገያችን በፊት ያለው ዛሬ ነውና ዛሬን በሚገባ መጠቀም ከእኛ ይጠበቃል! ዛሬን ከተጠቀምበት፣ ነገ ደግሞ በተራው እኛን ይጠቅመናል! ዛሬ የዘራነው ለነገ ይበቅላል! ዛሬ የሰጠነው ነገ ይመለሳል!

ታውቃላችሁ፣ ጊዜ ዕድል ነው! ለዛሬ ቀን መድረስ፣ ዛሬን ማየት ዕድል ነው! ዛሬን እየተመኙ ዛሬን ያላዩ፣ መኖር እየፈለጉ መኖርን ያልቻሉ ብዙ አሉ፡፡ ከተኙበት አልጋ ያልተነሱ፣ ከታሰሩበት ያልተፈቱ ብዙ ሰዎች አሉ! ወዳጄ ሆይ፣ እርስዎ በሕይወት የመኖር ዕድል ተሰጥትዎታል! በዚህ በተሰጠዎት ቀን ደግሞ ተግተው እንዲሠሩ ዕድል ተሰጥትዎታል! ነገር ግን በተሰጠዎት ዕድል ጊዜዎትን እንዴት እየተጠቀሙበት ነው?

ታውቃላችሁ፡ እያንዳንዱ ዕለት በዕድሜያችን ላይ የተጨመረ የእግዚአብሔር ስጦታ ነው! ይህንን ስጦታ በሚገባ እንድንጠቀምበት ያስፈልጋል! ጊዜ ውድ ነው! ሳንደርስ ሲናገር ‹‹ለቀኖች ጥንቃቄ የምንወስድላቸው ከሆነ ዓመታቶች ለራሳቸው ጥንቃቄ ይወስዳሉ›› ብሏል፡፡ እውነቱን ነው! የነገው ዘመን የሚወሰነው በዛሬው ጊዜያችን ነው! የዛሬን ጊዜ በአልባሌ ሁኔታ የምናባክን ከሆነ ነገ የባከነ ይሆናል፡፡ ዛሬን በሚገባ ከተጠቀምበትን የነገው ዘመናችን የተባረከ ይሆናል!

ወዳጄ ሆይ፣ ብዙ በመዝናናት ዛሬን ካሳለፉ፣ በየካፌ በየመዝናኛው ጊዜን ካቃጠሉ ያቃጠሉት ጊዜ ነገ ቀን ጠብቆ ያቃጥልዎታል! ዛሬን ሲዝናኑበት ነገ ይዝናናብዎታል፡፡ ዛሬ እንደ ቀለዱበት ይቀልድብዎታል፡፡ በጊዜ ሳይሰሩ፣ በጊዜ ሳይነቁ ንቀውና ረስተው ያሳለፉትን ቀን ነገ ግን በቁጭት በሐዘን ያስታውሱታል! ቀን ሳለ ሳይሰሩ፣ ጊዜ ሳለ ሳይጥሩ በቸልታ ያጠፉት ጊዜ ነገ ቀንዱን አብቅሎ፣ ጥፍሩን አሹሎ ይመጣብዎታል! ሳማና፣ እሾኹን፣ ብርድና ሐሩሩን አስከትሎ የገቡበት ገብቶ እረፍት ይነሳዎታል፡፡

ወገኖች ሆይ፣ ጉንዳኖች ዛሬ ላይ ቆመው ነገን ይመለከታሉ! የዛሬውን ጊዜ በመጪው ዘመን መነጽር ይቃኛሉ! ዛሬ አገኘን ብለው በልተውና ጠጥተው ወዲያው አይጨርሱም፡፡ በምቹ ጊዜ የሰበሰቡትን ለማይመቸው ጊዜ ያስቀምጡታል፡፡

ወገኖች ሆይ፣ ገንዘብ ስንይዝ፣ የሀብት ዕድል ስናገኝ ዛሬውኑ አንጨርስ! መጨረስ ካለብን መጨረስ ያለብን ነገ ሊጠቅመን በሚችል ነገር ላይ ይሁን! ለጌታ በመስጠት፣ ቤተክርስቲያን በመትከል፣ በትምህርት ላይ፣ በንግድ በኢንቨስትመንት፣ ልጅ በማሳደግ ላይ፣ ሀብት ንብረት በማፍራት ላይ እናውለው! እነዚህ ነገሮች ብድራት አላቸው! ነገ በቅለው አድገው አፍርተውና በዝተው መልሰው ይመለሱልናል!

ወገኖች ሆይ፣ ብዙዎቻችን ደግሞ ጊዜ አጣሁ፣ ጊዜ የለኝም እያልን መሥራት የሚገባንን ነገር ለነገ ስንገፋ ይታያል፡፡ በዚህም ምክንያት የኋላ ኋላ ዋጋ እንከፍላለን! እስኪ ልብ እንበል! አትሌት ኃይሌን አስቡ! ባራክ ኦባማን አስቡ! ቢል ጌትስንም አስቡ:᎓ እነዚህ ሰዎች ጊዜን ከየት አመጡ? ልክ እንደ እኛው በቀን ሀያ አራት ሰዓት ብቻ ነው ያላቸው! ሥራቸውንም እዩ፡ ፍሬያቸውንም እዩ! ያለቻቸውን ጊዜ ባግባቡ በመጠቀማቸው ምክንያት ብቻ ዛሬ ለደረሱበት ደረጃ የበቁት!

ወገኖች ሆይ፣ የለበስነውን ልብስ እንይ፣ የተጫማነውን ጫማ፣ ያነገትነውን ቦርሳ፣ የያዝነውን ሞባይል እንይ! እነዚህ ሁሉ የትጉሃን ሠራተኞች ውጤት፣ ጊዜያቸውን ባግባቡ የተጠቀሙ ሰዎች ፍሬ ናቸው!

ታውቃላችሁ፣ ጊዜ ሀብት ነው! ጊዜ ቅርስ ነው! ጊዜ ንግድ ነው፣ ኢንቨስትመንት ነው! ስለሆነም፣ ሀብትና ቅርሳችን፣ ንግድ፣ ኢንቨስትመንታችን እንዴት እንደያዝነው ራሳችንን እንጠይቅ! ጊዜን ከሚበላ አላስፈላጊ ነገር ራሳችንን እንቆጥብ! መኝታ አናብዛ፣ ጓደኛ አናብዛ፣ መዝናኛ አናብዛ! ሁሉ በልክ ይሁን! ለሥራችን ሁሉ መርሐ ግብር ይኑር፡፡ እንደቅደም ተከተሉ ጊዜን እንጠቀም! ዛሬ ጊዜ ሳለ ከጉንዳን እንማር!

ታውቃላችሁ፣ ሰው ልጅ ጊዜያዊ አበባ ነው፡፡ መልክና ውበትም ወዲያው ረጋፊ አበባ ነው! አግብቶ ለመውለድ፣ ወልዶም ለማሳደግ ወርቃማው ጊዜ የወጣትነት ወቅት ነው፡፡ ነገር ግን ብዙ ወጣቶች ሥራ እያማረጡ፣ ሰው እያማረጡ፣ አገር እያማረጡ ውድ የወጣትነት ጊዜያቸውን ያበላሹታል፡፡ መኪና ካልገዛሁ፣ መኖሪያ ካልሠራሁ፣ እያሉ በጊዜያቸው ይጫወቱበታል! ኋላ ላይ፣ መኪናው ተረስቶ፣ ትዳሩም ቀርቶ በቁጭት ማሳለፍ ይመጣል፡፡

ታውቃላችሁ፣ በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች የራሳቸው መኖሪያ ቤት ሳይኖራቸው አግብተው ወልደዋል፣ ወልደውም ከብደዋል! በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችም መኪና ሳይኖራቸው፣ መኪና ካላቸው ሰዎች እኩል ጧት ከቤት ወጥተው፣ ሥራቸውን ሠርተው ማታ ወደቤታቸው ይመለሳሉ!

ቤት መሥራቱም ሆነ፣ መኪና መግዛቱ አንድም የራዕይ ጉዳይ፣ አሊያም የዕድል ጉዳይ ነው! ዕድለኛው ሰው ወይ በተአምር፣ ወይንም በሎተሪ ወይንም በውርስ መኪናና ቤት ሊያገኝ ይችላል! ባለራዕዩ ደግሞ ጊዜውን ተጠቅሞ፣ ተግቶ በመሥራት ለራሱ ብዙ ዕድል መፍጠር ይችላል! ለኮንዶሚኒየም በመመዝገብ፣ በሥራ ፈጠራ፣ በአነስተኛና ጥቃቅን፣ አክሲዮን በመግዛት፣ ዕቁብ በመጣልና በመሳሰሉት፣ ገንዘብ መቆጠብ ይቻላል!

ታውቃላችሁ፣ ብዙ ወጣቶች በወላጆቻቸው ቤት ተመችቷቸው ስለሚኖሩ በኮንዶሚኒየም ምዝገባ ጊዜ ቆመው ሲያንቀላፉ ይታያል! በእጃቸው ያለውን አነስተኛ ገቢ በመመልከት፣ ከዚያች ላይ ቀንሶ ለቤት መቆጠብ ተራራ የመውጣት ያህል ከብዶ ይታያቸዋል! በወላጆቻቸው ቤት ሳሉ ለቁጠባ ምቹ የሆነ ጊዜን በከንቱ ያባክኑታል! ፋሽን በመከተል፣ ዕቃ በመቀየር፣ ዓለማቸውን ሰሲቀጩ ጊዜን ይገድሉታል! ስለሆነም ከጉንዳን እንማር!

 -------------------------------

(ይህን ዕለታዊ ዲቮሽን ላይክና ሼር ያድርጉ፣ ወዳጅ ጓደኞችዎም እንዲያገኙ ያግዙ፡፡ ዲቮሽኑ ሳይቋረጥ ዓመቱን ሙሉ እንዲቀጥል በጸሎትዎና ጌታ በልብዎ በሚያስቀምጥ ማናቸውም ነገር ሁሉ ይደግፉ፡፡ ጌታ ይባርክዎ፡፡)

No comments:

Post a Comment