Monday, October 13, 2014

ከገብረ ጉንዳን እንማር (#2) ….. ራስን ችሎ መሥራት!

ዲቮሽን ቁ.33/07     ሰኞ፣ ጥቅምት 3/07 ዓ.ም.  
(በመጋቢ ተስፋሁን ሐጢያ)



ከገብረ ጉንዳን እንማር (#2) ….. ራስን ችሎ መሥራት!


አንተ ታካች፥ ወደ ገብረ ጕንዳን ሂድ፥ መንገድዋንም ተመልክተህ ጠቢብ ሁን። አለቃና አዛዥ ገዢም ሳይኖራት መብልዋን በበጋ ታሰናዳለች፥ መኖዋንም በመከር ትሰበስባለች።…(ምሳ 6፡6-8)።

መሥሪያ ቤቶች ከበር ጥበቃ ጀምሮ በየስራ ክፍሎቹ አለቆችን ያስቀምጣሉ፡፡ ሠራተኞች በአለቆቻቸው መመሪያ መሠረት የተመደበላቸውን ይሠራሉ፡፡ ይህ ሁሉ ሆኖ፣ በርካታ ቦታ ላይ እንደሚስተዋለው የሚጠበቀው ያህል ሥራ አይሠራም፡፡

በጉንዳኖች ዘንድ አለቃ፣ አዛዥ፣ ገዥ፣ የለም፡፡ ቀስቃሽ፣ አንቀሳቃሽ፣ ተቆጣጣሪ፣ አስተባባሪ ሳያስፈልጋቸው ራሳቸውን ችለው ይሠራሉ፡፡ ቦርድ ወይም ኮሚቴ፣ ሰብሳቢ ወይም ጸሐፊ የላቸውም፡፡ መተዳደሪያ ደንብም ሆነ የሠራተኛ መመሪያ የላቸውም፡፡ ሆኖም፣ ራሳቸውን ችለው፣ ሥራቸውን በግል ተነሳሽነት በከፍተኛ አፈጻጸም ያከናውናሉ፡፡

ራስን ችሎ መሥራት ጆን ሲ ማክሴል ሲናገር ‹‹The First People that You Lead is Yourself›› ይላል፡፡ ከሁሉ አስቀድመህ የምትመራው ሕዝብ ራስህን ነው›› ማለቱ ነው፡፡ እውነት ብሏል! እነ አበበ ቢቂላ፣ እነ ኃይሌ ገብረሥላሴ፣ እነ ደራርቱ ቱሉ፣ እነ መሠረት ደፋር፣ እነ ጥሩነሽ ዲባባ … ራሳቸውን ለዓላማቸው በማስገዛታቸው ነው ለዓለም የተረፉት! ብርድ ሙቀት ሳይመርጡ በሌሊት ተነስተው በየተራራውና ጫካው ባይሮጡ፣ ስለሚበሉትና ስለሚጠጡት ነገር ሁሉ ዲስፕሊን ባይመርጡ ለውጤት አይበቁም!

ታውቃላችሁ፣ ከፍተኛ ሥራ ለመሥራት ከፍተኛ የሆነ የግል ተነሳሽነት ያስፈልጋል፡፡ ሺህ ጊዜ ሺህ የሰዓት ቁጥጥር ቢኖር፣ እልፍ ጊዜ እልፍ የኃላፊ ቁጥጥር ቢበዛ፣ ያለ ሠራተኛው የግል ተነሳሽነት የሚፈለገው ሥራ በሚፈለገው አፈጻጸም ሊከናወን አይችልም! ራስን ችሎ መስራት የግል ተነሳሽነትን ይጠይቃል!

ታውቃላችሁ፣ የግል ተነሳሽነት የሚመጣው ከራዕይ ነው! በዓለማችን ላይ ለውጥ ያመጡ ግለሰቦች ባለራዕዮች ናቸው! አብርሃም ከኬለዳዊያን ኡር የወጣው በራዕይ ነው፡፡ ዮሴፍ የግብጽ አገር ጠቅላይ መሪ የሆነው በራዕዩ ምክንያት ነው! ጀርመናዊው ማርቲን ሉተር የፕሮቴስታንት ተሐድሶ የወለደው በራዕይ ነው! ጥቁር አሜሪካዊው ማርቲን ሉተር ኪንግ  የጥቁሮች እኩልነት ያመጣው በራዕይ ነው! የወንጌል ሰባኪው ቢሊ ግርሃም፣ የኮምፒውተር(ማይክሮሶፍት) ፈልሳፊው ቢል ጌትስ፣ የፌስቡክ ፈጣሪው ማርክ ዙከርበርግ ባለራዕዮች ናቸው!

ወገኖች ሆይ፣ ለምንሰራው ነገር ራዕይ ይኑረን! ሰርቶ ለመለወጥ ራዕይ ይኑረን! ለራዕያችን ስኬት ተነሳሽነት ይኑር! ሠርቶ ለመለወጥ ብርቱ ራዕይ ካለ፣ ለዚህም ብርቱ ራዕይ ተነሳሽነት ካለ የሚሠራው ስራ ሸክም ሳይሆን መዝናኛ ይሆናል! ስራ መዝናኛ ሲሆን ውጤቱ ጎተራ ይሆናል!
 --------------------------------------------

 (ይህን ዕለታዊ ዲቮሽን ሼር ያድርጉ፣ ወዳጅ ጓደኞችዎም እንዲያገኙ ያግዙ፡፡ ዲቮሽኑ ሳይቋረጥ ዓመቱን ሙሉ እንዲቀጥል በጸሎትዎና ጌታ በልብዎ በሚያስቀምጥ ማናቸውም ነገር ሁሉ ይደግፉ፡፡ ጌታ ይባርክዎ፡፡)

No comments:

Post a Comment