Saturday, June 13, 2015

ኃይሌ!!!!

ዲቮሽን 277/07 እሁድ ሰኔ 7/07
(በእህት ማርታ ሲሳይነህ)

ኃይሌ!!!!

“ጌታ እግዚአብሔር ኃይሌ ነው!” ዕንባቆም 3፡19

አንዳንዴ ያለንበት ነባራዊ ሁኔታ፣ ወይም የተጫነን ወቅታዊ ስሜት፣ በስጋችንም በነፍሳችንም ዝለት እንዲሰማን
ያደርጋል። አስተዳደጋችን፣ እድሜያችን፣ የትምህርት ደረጃችን፣ የምናሳየው ባህሪ፣ የተሰበክነው ስብከት፣ ያነበብናቸው መጻህፍት፣ ያለንበት መልክዓምድራዊ አቀማመጥ፣ ሰዎች እንዲህ ናችሁ ብለው ያስቀመጡብን ስያሜ፣ ብቻ እጅግ በጣም እልፍ አእላፋት ነገሮች ---- ተጠራቅመው፡ ‘አልችልም፤ እኔ እንዲህ አይደለሁም፤ ይህን ለማድረግ ብቃት የለኝም፣ ይህ ሁኔታ ከባድ ነው’፣ እና የመሳሰሉትን አሉታዊ ነገሮች በራሳችን ላይ እንድናውጅ ያደርጉናል።

ግን ዕንባቆም ሲናገር እንዲህ አለ፡- ጌታ እግዚአብሔር ኃይሌ ነው፣ እግሮቼን እንደ ዋላ እግሮች ያደርጋል፣ በከፍታዎችም ላይ ያስሄደኛል። ዕንባቆም 3፡19

ዳዊትም ሲናገር: 2 ሳሙ 22: 34 እግሮቼን እንደ ብሆር እግሮች የሚያበረታ፥ በኮረብቶችም የሚያቆመኝ
እግዚአብሔር ነው።

ዛሬ፣ ለኔም ሆነ ለእናንተ ይህ የእንባቆም እና የዳዊት መንፈስ እንዲገባብን ጸሎቴ ነው። “ጌታ እግዚአብሔር ኃይሌ ነው! በአምላኬ ቅጥሩን እዘላለሁ።” እንድትሉና፣ እንድታደርጉትም ይኼው ጸለይኩ።

ከፍ ካሉብን ነገሮች በላይ እግዚአብሔር ያስኬደናል፣ ዳገት ከሆኑብን፣ ተራራ ከሆኑብን፣ ካደከሙን እና ካሰለቹን ነገሮች በላይ እግዚአብሔር ትልቅ ነው። እግዚአብሔር ኃይላችን ነው፣ ብርታታችን ነው።

መንፈስ ቅዱስ ሆይ፣ አንተ ብርቱና ኃያል መሆንህን ነፍሳችን እንድታውቅ፣ ዛሬ በእያንዳንዳችን ላይ ና! ኢየሱስ ሆይ፣ የሚያበረታው መንፈስህ፣ ኃይል የሚሰጠው መንፈስህ ይውረድብን፣ እንደሌላ ሰው የሚያደርገው፣ ከልማድ ህይወት የሚያስወጣው፣ ከልማድ ኃጢያት እና ድካም የሚያዘልለው ያንተ ኃይል፣ አ----ሁ----ን ይፍሰስብን። ሰምተህኛልና ተባረክ። ኦ! ሀሌ ሉያ!!!!

ትምህርቱ ጠቅሞዎታል? እንግዲያውስ እባክዎ፣ ላይክ እና ሼር፣ ኮሜንትም ያድርጉ ። ጌታ ይባርክዎ!

No comments:

Post a Comment