Tuesday, May 5, 2015

እግዚአብሔር እንደ ተናገረው – ሲያስብና ሲያደርግ!



ዲቮሽን 237/07፣ ማክሰኞ፥ ሚያዚያ 27/07
(
በፓ/ር ተስፋሁን ሐጢያ)

እግዚአብሔር እንደ ተናገረው – ሲያስብና ሲያደርግ!

እግዚአብሔርም እንደ ተናገረው ሣራን አሰበ እግዚአብሔርም እንደ ተናገረው ለሣራ አደረገላት፡፡ ሣራም ፀነሰች፥ እግዚአብሔርም በተናገረው ወራት ለአብርሃም በእርጅናው ወንድ ልጅን ወለደችለት(ዘፍ 21፡1-2)።
ወዳጄ ሆይ፣ የዘገየብዎት ተስፋ ይኖርብዎት ይሆን! ጌታ የተናገረዎትን ሳይቀበሉ ዓመታት ነጉደው ይሆን? ከአብርሃምና ሣራ ይማሩ!
ወገኖች ሆይ፣ እግዚአብሔር ለአብርሃምና ሣራ ልጅ እንደሚሰጣቸው ተናገራቸው፡፡ ሆኖም፣ የተነገራቸው ተስፋ ቃል ሳይፈጸም ረዥም ዓመታት አለፉ፡፡ በዕድሜ እስኪገፉ፣ ልጅ ለመውለድ ከሚያስችል ዕድሜ እስኪያልፉ፣ እስኪያረጁና እስኪገረጅፉ ድረስ ጌታ ዝም አላቸው፡፡
ታውቃላችሁ፣ ጊዜው የረፈደብን፣ ዕድሉ ያመለጠን መስሎ ቢታየንም፣ በእግዚአብሔር ዘንድ ግን እንዲህ ብሎ ነገር የለም፡፡ በመሆኑም፣ እግዚአብሔር እንደ ተናገረው ሣራን አሰበ፣ እንደ ተናገረውም አደረገላት፡፡
ታውቃላችሁ፣ እግዚአብሔር የተናገረው ጊዜ ሲደርስ፣ ሣራ ለአብርሃም በስተእርጅናው ወንድ ልጅን ወለደችለት፡፡ ይህም በሕይወቷ ሣቅና ደስታን አመጣላት!
ታውቃላችሁ፣ እግዚአብሔር የተናገረው ጊዜ ሲደርስ፣ በሕይወታችን ሣቅ ይሆናል፡፡ ይኼ ሣቅ በእኛ ዘንድ ብቻ የሚቆም ሣይሆን ቀደም ብለው ለሚያውቁን ሁሉ የሚተላለፍ ይሆናል፡፡
ወገኖች በርታ እንበል፣ እግዚአብሔር የተናገረው ጊዜ ሲደርስ፣ እንታሰባለን፡፡ ይኼ መታሰቢያ ደግሞ ከሳቅ ጋር ታጅቦ ወደእኛ ይመጣል፡፡ ሣራ በእግዚአብሔር ስትታሰብ፣ የተናገራትን ቃል አድርጎላታል፡፡ ይህም በስተእርጅና ልጅ መውለድና ማጥባት ነው፡፡ ይህን ስታደርግ፡ እርሷ ብቻ ሳትሆን ያየትና የተመለከታት ሁሉ በደስታ እንደሚስቅ ትመሰክራለች፡፡
ወዳጄ ሆይ፣ ጌታን ይጠብቁ! ጊዜ ረዘመ ብለው ሌላ ስህተት አይሥሩ! እግዚአብሔር  የገባልዎትን ቃል ጊዜው ሲደርስ፣ የሚያስብና የሚያደርግ አምላክ ነው! እግዚአብሔር እንደ ተናገረውሲያስብና ሲያደርግ ደግሞ ሐዘንና ለቅሶ ተረስቶ፣ ሐሴትና ደስታ፣ ሣቅና ፌሽታ ይሆናል!

No comments:

Post a Comment