Sunday, April 5, 2015

ደሙን ባየሁ ጊዜ – ከእናንተ አልፋለሁ !

ዲቮሽን . 207/07 እሁድ፥ መጋቢት 27/07 ..
(
በፓ/ር ተስፋሁን ሐጢያ)


ደሙን ባየሁ ጊዜ ከእናንተ አልፋለሁ !

ደሙም ባላችሁበት ቤቶች ምልክት ይሆንላችኋል፣ ደሙንም ባየሁ ጊዜ ከእናንተ አልፋለሁ፤ እኔም የግብፅን አገር በመታሁ ጊዜ መቅሰፍቱ ለጥፋት አይመጣባችሁም (ዘጸ 12፡13)። 

በብሉይ ኪዳን የእስራኤል ማኅበረ ምዕመናን ከግብጽ ከባርነት ምድር ሲወጡ፣ የማለፍ በዓል ወይም የፋሲካ በዓል አደረጉ፡፡ በዚህ የማለፍ በዓል ወይም የፋሲካ በዓል ላይ ነውር የሌለበትን የበግ ወይም የፍየል ጠቦት አርደው ደሙን ፋሲካውን በሚበሉበት ቤት ሁለቱን መቃንና ጉበኑን እንዲቀቡ ተነገራቸው – እንደተነገራቸውም አደረጉ!

እስራኤላዊያን የማለፍ በዓል ወይም የፋሲካ በዓል እንዲበሉ የታዘዙት ወገባቸውን ታጥቀው፥ ጫማቸውን በእግራቸው አድርገው፥ በትራቸውንም በእጃቸው ይዘው እንዲበሉ ተነገራቸው – እንደተነገራቸውም አደረጉ!

እስራኤላዊያን ሁሉ ይህን የማለፍ በዓል ወይም የፋሲካ በዓል ለእነርሱና ለልጅ ልጆቻቸው ለዘላለም ሥርዓት አድርገው እንዲጠብቁ ተነገራቸው – እንደተነገራቸውም አደረጉ!

በአዲስ ኪዳን ደግሞ ነውርና እድፍ የሌለበት የእግዚአብሔር በግ ኢየሱስ ክርስቶስ ፋሲካችን ሆኖበጎልጎታ መስቀል ታርዶልናል! የአዲስ ኪዳኑ ፋሲካችን ጌታችንና ‹‹መድኃኒታችን›› ኢየሱስ ክርስቶስ የሞተው ለድነታችንለኃጢአታችን ስርየትና ለሥጋ ፈውሳችን ነው! (ኢሳ 535 ማቴ 816-17 ያዕ 515)

ወገኖች ሆይ፣ የጌታችንና ‹‹መድኃኒታችን›› የኢየሱስ ክርስቶስ ደም የፈሰሰው ለኃጢአታችንና ለሕመማችን ድነት ብቻም ሳይሆን፣ ከማናቸውም አጋንንታዊ ጥቃቶችም እንድንድን ነው!

ይህ ሣምንት አብዛኛው የዓለማችን ክፍል የጌታችንንና የመድኃኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ሞትና ትንሣኤ በዓል የሚያከብርበት ወቅት ነው፡፡ የዚህ በዓል ዋነኛ ትኩረት ለድነታችን የፈሰሰውን የኢየሱስ ክርስቶስን ደም በሕይወታችን ከፍ አድርገን የምንይዝበት መሆን ይገባዋል! የዚህ በዓል ትኩረት በግብጽ አገር መቅሰፍቱ በመጣ ጊዜ የደሙ ምልክት የሌለበትን ሲያጠፋ የደሙ ምልክት ያለበትን ትቶ ያለፈበት የፋሲካ ትርሁም ሊገባን ይገባል!

ወገኖች ሆይ፣ ፋሲካችን ክርስቶስ በመስቀል ላይ ያፈሰሰው ደሙ ለሙሉ ድነታችንማለትም ከኃጢአት፣ ከሥጋ ሕመም፣ ከአጋንንት ጥቃት ሊያድነን ነው! በመሆኑም ይህንን በማወቅ የክርስቶስ ኢየሱስ ደም የማያነጻው ኃጢአት የለምና፣ ደሙን እየጠራን ከኃጢአታችን እንድንታጠብ፣ ደሙን እየጠራን ለማናቸውም ደዌና ሕመም እንድንፈወስ፣ እንዲሁም ደሙን እየጠራን ከማናቸውም አጋንንታዊ ጥቃቶች እንዳን!


ወገኖቼ ሆይ፣ ከኃጢአት፣ ከሥጋ ሕመምና ከማናቸውም አጋንንታዊ ጥቃቶች የሚያድነን የደሙ ምልክት በራሳችን ላይ አለን

No comments:

Post a Comment