ዲቮሽን
ቁ.160/07፣
ማክሰኞ፥
የካቲት
10/07 ዓ.ም.
(በፓ/ር ተስፋሁን ሐጢያ)
(በፓ/ር ተስፋሁን ሐጢያ)
ልጁን
እንድንመስል!
እግዚአብሔርንም ለሚወዱት እንደ አሳቡም ለተጠሩት ነገር
ሁሉ ለበጎ እንዲደረግ እናውቃለን (ሮሜ 8፡26-28)።
የተጠራነው ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን እንድንመስል ነው! የተጠራነው
እግዚአብሔርን እንድንወድድ፣ እንደ ሐሳቡም እንድንኖር ነው፡፡ እግዚአብሔርን መውደድ ማለት እኛ የምንወድደውንና አጥብቀን የምንፈልገውን
ነገር ለጌታ አሳልፈን በመስጠት ለጌታ ፈቃድ መኖር ማለት ነው፡፡ የተጠራነው ሁሉን ለጌታ ለመተው ብቻም አይደለም፡፡ የተጠራነው
ልጁን እንድመስል ነው!
ወገኖች ሆይ፣ የተጠራነው ኢየሱስ ክርስቶስን እንድንመስል
ነው! ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የአባቱን ፈቃድ ለመፈጸም ለአባቱ ታዝዞ ክብሩን ትቶ፣ ከዙፋኑ ወርዶ አገልጋይ ሆነ፡፡ የአባቱን
ፈቃድ ለመፈጸም መከራና ችግር እየተቀበለ፣ ለሰው ልጆች ሁሉ የእግዚአብሔርን ፍቅር፣ የመንግሥቱን ሥራ እየመሰከረ በዚህ ምድር
ላይ ተመላለሰ፡፡
የአባቱን ፈቃድ ለመፈጸም በምድር ላይ ሲመላለስ እየተራበና
እየተጠማ፣ እየቀሰለና እየደማ፣ እያለቀሰና እንባውን እያፈሰሰ በዚህች ምድር ላይ ተመላለሰ፡፡ የአባቱን ፈቃድ ለመፈጸም እየተሰደደ፣
እየተሰደበ፣ እየተዋረደ ተመላለሰ፡፡ መከራን እየተቀበለ፣ ሁሉን በትዕግሥት እያለፈ በዚህች ምድር ላይ ተመላለሰ፡፡
ወገኖች ሆይ፣ የአባቱን ፈቃድ ለመፈጸም በሐሰት ተከሰሰ፣ ያለ
በደልና ጥፋቱ በአሰቃቂ ሁኔታ ተገረፈ፣ የተረገመ ሰው በሚቀጣበት ቅጣት ያለ ምንም ኃጢአቱ በመስቀል ላይ ተሰቀለ፣ ሞተ፣
ተቀበረ!
ወገኖች ሆይ፣ የተጠራነው ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን
እንድንመስል ነው! ለአባታችን ፈቃድ ፈቃዳችንን አስገዝተን፣ የምንወድደውን ነገር ለእርሱ አሳልፈን ሰጥተን፣ ኢየሱስ ክርስቶስን
በመምሰል በዚህች ምድር ላይ እንድንመላለስ ነው!
ታውቃላችሁ፣ የተጠራነው ወደዚህ መረዳት፣ ልጁን ወደማወቅ
እውቀት እንድንደርስ ነው! የተጠራነው ወደዚህ ልጁን ወደ መምሰል ዕውቀት፣ ወደ መለኮታዊ ኅብረት ነው!
ታውቃላችሁ፣ ልዩ ልዩ ፈተናዎች በሕይወታችን ሲያልፉ ልጁን
እንድንመስል እየተሠራን ነው! በመከራና ችግር፣ በእሳትና ውሃ መካከል ስንሄድ፣ ወይንም በማናቸውም ተግዳሮት መካከል ስንሄድ ልጁን
እንድንመስል እየተሠራን ነው!
ታውቃላችሁ፣ መከራና ችግር እኛን እንዲሠሩ እንዲቀርጹ
እንጂ እኛን እንዲያጠፉ ጌታ አይፈልግም! ያለ ጌታ ፈቃድ፣ ያለ እርሱ እይታ ወደ እኛ የሚመጡ ተግዳሮቶች የሉም፡፡ ያለ እርሱ
ቁጥጥር፣ ከእርሱ እይታ ውጭ ወደ እኛ የሚመጡ ተግዳሮቶች የሉም፡፡ እርሱ የማይፈታው፣ ከችሎታው በላይ የሆነ ነገር በምድር
ቢሆን በሰማይ፣ ወይንም በየትኛውም ዓለም የለም፡፡ ከእርሱ የተሰወረ ምንም ፍጥረት የለም፡፡
ወገኖች ሆይ፣ በሕይወታችን ከሚያጋጥሙን ነገሮች መልካምን
ሊያወጣ፣ እንድናድግበት እንጂ፣ እንድንወድቅበትና እንድንጠፋበት ጌታ አይፈልግም! ስለሆነም፣ በሕይወታችን የሚያልፉ ጥሩም ሆኑ
ክፉ ነገሮች ሁሉ አንድ ላይ ተያይዘው ለጥቅማችንና ልጁን እንድንመስል የሚቀርጹን እንደሆኑ እናውቃለን!
ፈተና ሲበዛ መዛልም አለና፣ መከራ ከብዶብን ዝለን
እንዳንወድቅ፣ መንፈስ ድካማችንን ያግዛል! በመከራችን ጊዜ፣ በመሠራታችን ወቅት እንዴት እንድንጸልይ እንደሚገባን አናውቅምና፥ መንፈስ
ቅዱስ ራሱ በማይነገር መቃተት ስለ ቅዱሳን ሁሉ ዘወትር ይማልዳል! ስለሆነም፡ ልባችን በጌታ ይጽናና!
No comments:
Post a Comment