Monday, February 16, 2015

ከቀጨጩ ሕልሞች - ይጠንቀቁ!

ዲቮሽን .159/07 ሰኞ፥ የካቲት 9/07
(በፓ/ር ተስፋሁን ሐጢያ)



ከቀጨጩ ሕልሞች - ይጠንቀቁ!


እነሆ፥ በሕልሜ በወንዝ ዳር ቆሜ ነበር፡፡ እነሆም ስጋቸው የወፈረ መልካቸውም ያማረ ሰባት ላሞች ወጡ፥ በመስኩም ይሰማሩ ነበር፡፡ ከእነርሱም በኋላ እነሆ የደከሙ መልካቸውም እጅግ የከፋ ስጋቸውም የከሳ ሌሎች ሰባት ላሞች… ወፍራሞቹን … ዋጡአቸው… በሆዳቸውም እንደተዋጡ አልታወቀም፥ መልካቸውም በመጀመሪያ እንደነበረው የከፋ ነበረ (ዘፍ 41)፡፡


የሰው ልጅ በወንዝ ዳር እንዳለ ተክል ነው፡፡ ሊለመልምና - ሊሰፋ፥ ሊያብብና - ሊያፈራ የሚያስችሉ ሰፊ ዕድሎች በዙሪያው አሉት! ተምሮ - ሊመረቅ፥ ሰርቶ - ለመበልጸግ፥ ነግዶ - ሊያተርፍና፥ ታግሎ - ለማሸነፍ የሚያስችሉ በሽበሽ ዕድሎች በዙሪያው አሉት! ነገር ግን ብዙ ጊዜ እንደሚስተዋለው የቀጨጩ ሕልሞች እነዚህን ዕድሎች ሲያሸንፉ፥ ወደጎን ሲገፉ እና ሲያጨናግፉ ይታያል! 


ወገኖች ሆይ፥ የሰው ልጆች ሁሉ በዕድል ሙሽሮች፥ በስጋት ሚዜዎች የታጀቡ ናቸው፡፡ የሰው ልጆች ሁሉ በግራ ቀኛቸው በሳቅና ደስታ፥ በለቅሶና እንባ የታጀቡ ናቸው፡፡ ክብርና - ውርደት፥ መውጣትና - መውረድ፥ ቀንና ሌሊቱ፥ በጋና - ክረምቱ፥ አብረውን የሚኖሩ የሁልጊዜ ዘመድ ወዳጆቻችን ናቸው!


ታውቃላችሁ፥ መኖርና - መሞት፥ መራብና - መብላት፥ መውደቅና - መነሳት፥ ሐዘንና _ ደስታ አብረውን የሚኖሩ የሁልጊዜ ዘመድ ወዳጆቻችን ናቸው!


ወገኖች ሆይ፥ ብዙ ጊዜ የሕይወት ትርጉሙ ውሉና ሚዛኑ ግራ ይገባናል! የሕይወትን ክንፎች አንዱን ይዘን አንዱን ጥለን ለመብረር ስንሞክር እንደናቀፋለን! የሕይወትን ጭብጨባ በአንድ እጃችን ብቻ ማጨብጨብ ስንፈልግ ተስፋ እንቆርጣለን!


ወዳጄ ሆይ፥ "አለኝ ብለህ አትኩራ - አጣሁ ብለህ አትፍራ፥ አታውቀውምና - የአምላክን ስራ" የሚለውን ብሂልም ያስቡ! ከቀጨጩ ሕልሞች ራስዎን ይጠብቁ!


ወዳጄ ሆይ፥ ከፊደሎቻችን ይማሩ! የፊደሎቻችን የመጀመሪያው ገበታ "ሀ፥ ሀ፥ ሀ" ብሎ ጀምሮ፥ "ፐ፥ ፐ፥ ፐ" ብሎ የአድናቆት ዜማ አቅርቦ ሲጨርስ፥ ሁለተኛው የፊደል ገበታ ደግሞ "ቋ፥ ቷ፥ ኳ፥ ዷ፥ ጓ፥ ጧ፥ ጯ" የመሳሰሉ ጡጫዎች ይዟል፡፡ የሚገርመው ግን፥ ከእነዚህ ጉሽሚያዎች በኋላ ደግሞ "ፏ" መኖሯ ደግሞ፥ የሰው ልጅ ልዩ ልዩ የሕይወትን ጡጫዎች ታግሶ ካለፈና ካሸነፈ የሕይወት ፍጻሜ "ፏ" ያለ እንደሚሆን ይታመናል! ስለሆነም፥ ከቀጨጩ ሕልሞች ራስዎን ይጠብቁ!


ወዳጄ ሆይ፥ በሕይወት ፈተና፥ በፍርሃትና ስጋት ነፍስዎ ስትጨነቅ፥ ተስፋ አይቁረጡ! በማዕበል፥ በወጀብ ነፍስዎ ስትታወክ፥ ተስፋ አይቁረጡ! እስከመጨረሻዋ ዕለት፥ እስከ ትንፋሽዎ መቆም መቅዘፍ ይቀጥሉ! 


ወዳጄ ሆይ፥ ከቀጨጩ ሕልሞች ራስዎን ይጠብቁ! የቀጨጩ ሕልሞች የያዙትን ተስፋ፥ ያገኙትን ዕድል መዋጥ ሲጀምሩ እጅዎትን አይስጡ! የካቡት ተንዶ፥ የገነቡት ፈርሶ፥ ሕልምዎ እንዳይጨልም ጥንቃቄ ያድርጉ! ሕይወት "ሀ! ሀ!" እና "ፐ!ፐ!" ብቻ ሳትሆን፥ እነ "ቋ" ፥ እነ "ቷ" ፥ እነ "ኳ" ፥ እነ "ጧ" ፥ እነ "ጯ" ፥ እንዳሏት ያስቡ! ከእነዚህ የሕይወት ጡጫዎች በኋላም፥ እነ "ፏ" መኖራቸውን ማስታወሻ ይውሰዱ! ከቀጨጩ ሕልሞች ራስዎን ይጠብቁ!

No comments:

Post a Comment