Friday, December 5, 2014

የጴንጠቆስጤነት አቡጊዳ(#6) –ስነ ስብከት!

ዲቮሽን ቁ.86/07     አርብ፣ ሕዳር 26/07 ዓ.ም.
(በመጋቢ ተስፋሁን ሐጢያ)

የጴንጠቆስጤነት አቡጊዳ(#6) –ስነ ስብከት!


… ሰዎች ሆይ፥ ይህን ቃል ስሙ፤ ራሳችሁ እንደምታውቁ፥ የናዝሬቱ ኢየሱስ እግዚአብሔር በመካከላችሁ በእርሱ በኩል ባደረገው ተአምራትና በድንቆች በምልክቶችም ከእግዚአብሔር ዘንድ ለእናንተ የተገለጠ ሰው ነበረ፤ እርሱንም … በዓመፀኞች እጅ ሰቅላችሁ ገደላችሁት። እግዚአብሔር ግን የሞትን ጣር አጥፍቶ አስነሣው፥ ሞት ይይዘው ዘንድ አልቻለምና (የሐዋ 2፡22-24)።

ለጴንጠቆስጤነት ማንነት ሌላው መገለጫ ድንገተኛና እውነተኛ(authentic) የሆነ የቃሉ መገለጥ ወይንም ቃሉን መሠረት አድርጎ እንደወረደ የሚቀርብ መልዕክት ነው፡፡ የዚህ ድንገተኛና እውነተኛ የቃሉ መገለጥ መታወቂያው በመንፈስ ቅዱስ መነዳት የሚቀርብ የወንጌል ምስጢር ነው፡፡ የወንጌል ምስጢር ማለት ኢየሱስ ክርስቶስን በሙላት መስበክ ነው!

ወገኖች ሆይ፣ የጴንጠቆስጤ ስነስብከት የመዕልክቱ ጭብጥ በዋናነት በሦስት መሠረታዊ ነገሮች ላይ ያማከለ ነው! (1ኛ) የጴንጠቆስጤ ስብከት የመልዕክቱን ማዕከል ቃሉ ላይ ያደርጋል፡፡(2ኛ) የጴንጠቆስጤ ስብከት የመንፈስ ቅዱስ ኃይል ተሞልቶ ይቀርባል፡፡ (3ኛ) የጴንጠቆስጤ ስብከት ኢየሱስ ክርስቶስን ከፍ ከፍ ያደርጋል፡፡ መንፈስ ቅዱስ በሚሠራበት ቦታ ሁሉ የጊዜው ቃል(ሬማ) በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ተገልጦ በሙላት ይሰበካል፡፡ የጊዜው ቃል(ሬማ) በመንፈስ ቅዱስ ኃይል በሚሰበክበት ቦታ ሁሉ ኢየሱስ ክርስቶስ ይከብራል!

ታውቃላችሁ፣ መንፈስ ቅዱስ በሚሠራበት ቦታ ሁሉ የጊዜው ቃል፣ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ኢየሱስ ክርስቶስ ክብር እና በሙላት ስለሚሰበክ፣ ፍርሃትና ስጋት ጨርሶ ይጠፋል!

ወገኖች ሆይ፣ ጴጥሮስን ስብከት አስቡ! በጴንጠቆስጤ ዕለት በድንገት መንፈስ ቅዱስ ሲፈስስ ጴጥሮስ ማንንም ሳይፈራ በድፍረት ቆሞ የሰበከው ቃሉን(16)መንፈስ ቅዱስን (17-21) እና ኢየሱስ ክርስቶስ (22-36) ነው!

ወገኖች ሆይ፣ መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር እስትንፋስ ያለበት፣ በመንፈስ ቅዱስ ምሪት የተጻፈ ነውና፣ ለመስበክ ስንቆም ሌላ ሌላ ታሪክ፣ ሌላ ሌላ ተረት፣ ሌላ ሌላ ቀልድና ቧልት፣ ሌላ ሌላ ፍልስፍና፣ ሌላ ሌላ ዝመና ትተን፣ ከመንፈስ ቅዱስ ወቅታዊ ምሪት፣ ወቅታዊ መልዕክት ተቀብለን፣ በመንፈስ ቅዱስ ተሞልተን፣ በመንፈስ ቀዱስ ተቀብተን  ኢየሱስ ክርስቶስን ከፍ ከፍ የሚያደርግ የእግዚአብሔርን ቃል እንስበክ !

ወገኖች ሆይ፣ ቤተክርስቲያን የተመሠረተችው በመንፈስ ቅዱስ ነውና፣ በቤተክርስቲያን ውስጥ ማናቸውም አገልግሎታችን፣ ማናቸውም ትምህርታችን፣ ማናቸውም ጸሎታችን፣ ማናቸውም ዝማሬያችን፣ መንፈስ ቅዱስ ተኮር እንዲሆኑ እናድርግ!

ወገኖች ሆይ፣ የእምነታችን ጀማሪና ፈጻሚ፣ እንዲሁም ራስ ኢየሱስ ክርስቶስ ነውና ቤተክርስቲያን ውስጥ ማናቸውም አመራራችን፣ ማናቸውም አስተዳደራችን፣ ማናቸውም በጀታችን ማናቸውም እቅዳችን፣ ማናቸውም ነገራችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተኮር እንዲሆኑ እናድርግ!

ወገኖች ሆይ፣ የቤተክርስቲያናችን አገልግሎቶች ዋነኛ ማዕከል ቃሉ፣ ኢየሱስ ክርስቶስና መንፈስ ቅዱስ ሲሆን፣ በሚያስደምሙና በሚያስገርሙ ተአምራቶች፣ በድንቆችና በምልክቶች እንታጀባለን፡፡ ይህ እንዲህ ሲሆን፣ እንደ ደራሽ ውሃ በሚድኑ ነፍሳት እንጥለቀለቃለን፡፡ አሜን!

--------------------------------

(ትምህርቱ ጠቅምዎታል? እንግዲያውስ ላይክና ሼር ያድርጉ፣ ወዳጅ ጓደኞችም እንዲያገኙ ያግዙ፡፡ ጌታ ይባርክዎ!)

No comments:

Post a Comment