ዲቮሽን ቁ.85/07
ሐሙስ፣ ሕዳር 25/07 ዓ.ም.
(በመጋቢ ተስፋሁን
ሐጢያ)
የጴንጠቆስጤነት አቡጊዳ(#5) –ትንቢት መናገር!
እግዚአብሔር
ይላል። በመጨረሻው ቀን እንዲህ ይሆናል፤ ሥጋ በለበሰ ሁሉ ላይ ከመንፈሴ አፈሳለሁ፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁም ትንቢት
ይናገራሉ፥ ጎበዞቻችሁም ራእይ ያያሉ፥ ሽማግሌዎቻችሁም ሕልም ያልማሉ፡፡ ደግሞም በዚያች ወራት በወንዶችና በሴቶች ባሪያዎቼ ላይ
ከመንፈሴ አፈሳለሁ ትንቢትም ይናገራሉ። (የሐዋ 2፡17-18)፡፡
ለጴንጠቆስጤነት ማንነት ሌላው መገለጫ በምዕመናን መካከል
ትንቢት የመናገር ስጦታ መፍሰስ ነው፡፡ ጴንጠቆስጤዎች ትንቢት የሚናገሩት ከእግዚአብሔር አፍ ተቀብለው ነው፡፡ ለዚህም ነው፣
‹‹የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል›› የሚሉት፡፡ ይህም ማለት በድምጽ እየተናገረ ያለው እግዚአብሔር ራሱ ነው ማለት
ነው፡፡ ይህም ማለት፣ እግዚአብሔር ዛሬም በሕዝቡ መካከል ነው ማለት ነው፡፡
ወገኖች ሆይ፣ የእግዚአብሔር አፍ ሆኖ ለእግዚአብሔር ሕዝብ ትንቢት
መናገር የሚችለው ማነው? ድሆችና ባለጠጎች፣
ምሁራንና መሐይሞች፣ ትልልቆችና ትንንሾች፣ ወንዶችና ሴቶች፣ በአጠቃላይ ሥጋ የለበሰ የሰው ልጅ ሁሉ ነው! ይህ እንዴት ሊሆን
ይችላል? ይህ ሊሆ የሚችለው፣ ሥጋ
በለበሰ ሁሉ ላይ መንፈስ ቅዱስ ሲፈስስ ነው፡፡
ወገኖች
ሆይ፣ ሥጋ በለበሰ የሰው ልጅ ላይ፣ መንፈስ ቅዱስ ሲፈስስ ወንዶችና ሴቶች፣ ልጆችና አዋቂዎች፣ ወጣቶችና ሽማግሌዎች ሁሉ የሚሠሩት
ሥራ ይሰጣቸዋል፡፡ ያኔ፣ ትንቢት መናገሩ፣ ራዕይ መመልከቱ፣ ሕልምን መመልከቱ የሚቻል ይሆናል፡፡ መንፈስ ቅዱስ ሲፈስስ የማይሠራ
አካል፣ የማይጠቅም ብልት፣ የማይረባ ጅማት የለም፡፡ ሁሉም በየቦታው፣ ሁሉም በስጦታው የአካሉ አገልጋይ፣ የመንግሥቱ ተካይ ይሆናል፡፡
ወገኖች
ሆይ፣ ትንቢት መናገር በሁለት ይከፈላል፡፡ አንዱ ወቅታዊና የአሁኑን ነገር በቅጽበት መግለጥ ወይንም ማስታወቅ ሲሆን፣ ሁለተኛው
የወደፊቱን ክስተት አስቀድሞ መናገር ነው፡፡ የወቅቱን ወይንም የአሁኑን ነገር በቅጽበት መናገር በልማድ ቋንቋ ‹‹መገለጽ››
የምንለው ነው፡፡
ቅጽበታዊ
ትንቢት ‹‹መገለጽ›› በሰዎች ሕይወት የተደበቁና የተሸሸጉ ነገሮችን በመንፈስ ቅዱስ መነጽር ፈልፍሎ ማውጣት ነው፡፡ ወገኖች
ሆይ፣ ሰዎች በልባቸው ውስጥ ልዩ ልዩ ጥያቄ ይዘው፣ ሸክም ተሸክመው ወደ ጉባኤ ይመጣሉ፡፡ ይህን አይቶ የሚረዳ ጌታ ደግሞ መንፈስ
ቅዱስ በሚሠራበት ቦታ ሁሉ ላይ አለ፡፡ በመሆኑም፣ ሰዎች ለራሳቸው ብቻ ደብቀው የያዙትን የግል አጀንዳ በመግለጽ እና ተስፋ በመሙላት
ያጽናናቸዋል፡፡
ወገኖች
ሆይ፣ የትንቢት አገልግሎት ጉባኤውን ያንጻል፡፡ ለአንዱ የሚሰጥ ምልክት፣ በሌላው ሰው ልብ ውስጥ እምነትን ይዘራል፡፡ ለአንዱ የሚነገር
ትንቢት ሌላኛውን ያጽናናል፡፡ ስለሆነም፣ የትንቢት አገልግሎት እንዲያድግ ራሳችንን ለመንፈስ ቅዱስ ሥራ እናመቻች፡፡
--------------------------------
(ትምህርቱ
ጠቅምዎታል? እንግዲያውስ ላይክና ሼር
ያድርጉ፣ ወዳጅ ጓደኞችም እንዲያገኙ ያግዙ፡፡ ጌታ ይባርክዎ!)
No comments:
Post a Comment