Saturday, November 1, 2014

‹‹አምላክ የለም!››… ???

ዲቮሽን ቁ.52/07     ቅዳሜ፣ ጥቅምት 22/07 ዓ.ም.
(በመጋቢ ተስፋሁን ሐጢያ)

‹‹አምላክ የለም!››… ???

ሰነፍ በልቡ። አምላክ የለም ይላል። (መዝ 14፡1)

አንድ ቀን በእግዚአብሔር መኖር የማያምነውን Atheist ትንሽዬ ሴት ልጁ Dad, Where is God? (እግዚአብሔር የሚገኘው ዬት ነው?) ስትል ጠየቀችው፡፡ ኤቲስቱ አባቷም በጽሁፍ God is nowhere(እግዚአብሔር ዬትም አይገኝም) ብሎ መለሰላት፡፡

ልጁ በኮልታፋ አንደበቷ የአባቷን ጽሁፍ ስታነብ nowhere የሚለውን ጥምር ቃል ለሁለት ከፍላ God is now here (እግዚአብሔር አሁን እዚህ ነው) ብላ አነበበች፡፡ በዚህም የአላማኙ አባቷ ልብ እጅግ ተነካ! በገዛ ራሱ ጽሁፍና እጅግ በሚወዳት ትንሽዬ ልጁ አንደበት ባልጠበቀው ሁኔታ ልቡ የተነካው አላማኝ ለጌታ ተሸነፈ፡፡ በመሆኑም ‹‹የለም›› ይለው የነበረውን ጌታ ‹‹አለ›› ብሎ ለመቀበል ተገደደ!

ወገኖች ሆይ፣ አንዳንድ ሰዎች የፈጣሪን ሕልውና ለመቀበል የሚቸገሩት ለምን ይመስላችኋል? ፈጣሪ አለመኖሩን እርግጠኛ ስለሆኑ ነውን? በጭራሽ! ፈጣሪ አለመኖሩን አረጋግጠው ቢሆን ኖሮ ባልተጨነቁለት ነበር! ይልቁንም፣ ‹‹እግዚአብሔር የለም›› የሚሉቱ ‹‹እግዚአብሔር አለ›› የሚሉትን የሚያሳድዱበት ዋናው ምክንያት ራሳቸውን ሊሸሽጉ ከማይችሉት ሕልውናው የተነሣ ነው!

ወገኖች ሆይ፣ በሰው ልጆች ራስ ላይ እግዚአብሔር ‹‹ሕሊና›› የሚባል የሳተላይት ጣቢያ ተክሏል! ይህ ስቴሽን ሰዎች በሚሠሩት ክፉ ሥራ ይወቅሳቸዋል፣ ስለኃጢአታቸው ይከስሳቸዋል፣ እረፍት ይነሣቸዋል! በክፉ ሥራቸው የረከሱ ሰዎች በሕሊናቸው አማካይነት ጧት ማታ እየከሰሰ የሚኮንናቸው አምላክ መኖሩን ያውቁታል!

ወገኖች ሆይ፣ እግዚአብሔር አለ! የሚሠራ፣ የሚናገር፣ የሚለውጥ፣ የሚቀይር፣ የሚያይ የሚሰማ ጌታ በሁሉም ሥፍራ አለ! ቤታችንን ዘግተን የምንሠራውን፣ ከሰው ተሸሽገን የምናደርገውን፣ በምስጢር ደብቀን የምንይዘውን ነገር ሁሉ የሚያይ፣ የሚሰማ፣ ጌታ አለ!

ወዳጆች ሆይ፣ እግዚአብሔር በሁሉም ሥፍራ አለ! በመኖሪያ ቤታችን፣ በመሥሪያ ቤታችን፣ በንግድ ሱቃችን፣ በመደብራችን፣ በውሎ አዳር ቦታችንና በሁሉ ስፍራችን እግዚአብሔር አለ!

ወዳጆች ሆይ፣ በምንመካከርበት፣ በምንማማልበት፣ በምንዋዋልበት፣ በምንፈራረምበት ስፍራ ሁሉ እግዚአብሔር አለ!

-------------------------

(ይህን ዕለታዊ ዲቮሽን ላይክና ሼር ያድርጉ፣ ወዳጅ ጓደኞችዎም እንዲያገኙ ያግዙ፡፡ ጌታ ይባርክዎ!)

No comments:

Post a Comment