ዲቮሽን 238/07፣ ረቡዕ፥ ሚያዚያ 28/07
(በፓ/ር ተስፋሁን ሐጢያ)
(በፓ/ር ተስፋሁን ሐጢያ)
እግዚአብሔር –
እንዲህ ይላል!
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በሰው የሚታመን ሥጋ ለባሹንም ክንዱ የሚያደርግ ልቡም ከእግዚአብሔር የሚመለስ ሰው ርጉም ነው … በእግዚአብሔር የታመነ እምነቱም እግዚአብሔር የሆነ ሰው ቡሩክ ነው (ኤር 17፡5-8)።
አንዳንዴ በቤተሰቦቻችን ላይ፣ አንዳንዴም በወዳጅ ዘመዶቻችን ላይ፣ አንዳንዴም በአብሮ አደጎቻችን ላይ እምነት እንጥላለን! አንዳንዴ በባለሥልጣናት ላይ፣ አንዳንዴም በቤተክርስቲያን መሪዎች ላይ፣ አንዳንዴም በአገልጋዮች ላይ፣ አንዳንዴም ልባችንን ባሸነፈው ሰው ላይ እምነት እንጥላለን!
ወገኖች ሆይ፣ የሰው ልጅ ኑሮውን በሥራ አሸንፎ ባለጠጋ ሲሆን፣ ነፍሱን፣ ‹‹አንቺ ነፍሴ፥ ለብዙ ዘመን የሚቀር ብዙ በረከት አለሽ፤ ዕረፊ፥ ብዪ፥ ጠጪ፥ ደስ ይበልሽ›› ለማለት ይመኛል፡፡
ወገኖች ሆይ፣ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በሰው የሚታመን ሥጋ ለባሹንም ክንዱ የሚያደርግ፣ ልቡም ከእግዚአብሔር የሚመለስ ሰው ርጉም ነው!
ታውቃላችሁ፣ የሰውን ልጅ በማመን፣ ሥጋ ለባሹን ሰው ክንዳችን በማድረግ፣ ከእግዚአብሔር አምላክ ልባችንን መመለስ፣ እርግማን ያመጣል!
ወገኖች ሆይ፣ የሰውን ልጅ መታመን፣ በምድረ በዳ እንዳለ ቍጥቋጦ መሆንን ያመጣል፡፡ የሰውን ልጅ መታመን፣ መልካም በመጣ ጊዜ ከማየት ያግዳል! የሰውን ልጅ መታመን፣ ሰውም በሌለበት፥ ጨው ባለበት ምድር በደረቅ ምድረ በዳ ወስዶ ያስቀምጣል።
ወገኖች ሆይ፣ የሰው ልጅ ማኅበራዊ ፍጡር ነውና በልዩ ልዩ ማኅበራዊ ጥልፍልፎች ውስጥ ገብቶ ራሱን ማጠላለፍ ግዴታ ይሆንበታል፡፡ ወዳጅ ጓደኛ በመመሥረት፣ በልዩ ልዩ ማኅበራዊ ግንኙነቶች ውስጥ በመታቀፍና በመደራጀት፣ የሕይወትና የንብረት ዋስትና በመግዛት፣ ዕድር፣ ዕቁብና አክሲዮን በመግባት፣ ሀብትና ንብረት በማፍራትና ሌሎችም መሰል ነገሮች በማድረግ ኑሮውን በአስተማማኝ መሠረት ላይ የገነባ መስሎ ይሰማዋል!
ወገኖች ሆይ፣ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦በእግዚአብሔር የታመነ እምነቱም እግዚአብሔር የሆነ ሰው ቡሩክ ነው!
ወገኖች ሆይ፣ በእግዚአብሔር የታመነ፣ እምነቱም እግዚአብሔር የሆነ ሰው፣ በውኃ አጠገብ እንደ ተተከለ፥ በወንዝም ዳር ሥሩን እንደሚዘረጋ ሙቀትም ሲመጣ እንደማይፈራ ቅጠሉም እንደሚለመልም፥ በድርቅ ዓመትም እንደማይሠጋ ፍሬውንም እንደማያቋርጥ ዛፍ ይሆናል።
ወዳጄ ሆይ፣ በራሳችን መተማመን ትተን፣ እግዚአብሔር እንታመን፣ እምነታችንንም በእግዚአብሔር ላይ እናድርግ! ወገኖች ሆይ፣ የሰው ልብ ከሁሉ ይልቅ ተንኰለኛ እጅግም ክፉ ነውና፣ ማንም አያውቀውምና፣ በወዳጅ ዘመዶቻችን መተማመን ትተን፣ እግዚአብሔር እንታመን!
ወዳጄ ሆይ፣ እግዚአብሔር ለሰው ሁሉ እንደ መንገዱ፥ እንደ ሥራው ፍሬ ይሰጥ ዘንድ ልብን ይመረምራልና፣ ኵላሊትንም ይፈትናልና፣ በእግዚአብሔር እንታመን!
No comments:
Post a Comment