Thursday, January 22, 2015

ዝቅ፣ ከፍ – ዝቅ፣ ከፍ፣ ከፍ!

ዲቮሽን .134/07     ሐሙስጥር 14/07 ..
(በመጋቢ ተስፋሁን ሐጢያ)


ዝቅ፣ ከፍ – ዝቅ፣ ከፍ፣ ከፍ

እግዚአብሔር ድሀ ያደርጋል፥ ባለጠጋም ያደርጋል ያዋርዳል፥ ደግሞም ከፍ ከፍ ያደርጋል(1 ሳሙ 2፡7)።

ሰዎች ነንና፣ አግኝተን ስናጣ፣ ወጥተን ስንወርድ፣ ከብረን ስንዋረድ፣ ስቀን ስናለቅስ እጅግ ይከፋናል፡፡ ሰዎች ነንና፣ የሞላው ሲጎድል፣ የሰፋው ሲጠብብ፣ እጅግ ይከፋናል፡፡

ወገኖች ሆይ፣ ከላይ የቀረበው ጥቅስ ልዑል የሆነው እግዚአብሔር፣ በሰማይ ሠራዊት፣ በምድርም ላይ በሚኖሩ መካከል እንደ ፈቃዱ የሚያደርግ መሆኑን፣ እጁንም የሚከለክላት ወይም ‹‹ምን ታደርጋለህ?›› የሚለው የሌለው መሆኑን ጮኾ ይናገራል!

ወገኖች ሆይ፣ ካላይ የተነበበው ጥቅስ፣ እጁ ተይዞ ‹‹ምን ታደርጋለህ?›› የማይባለው ይኼ ልዑል አምላክ፣ በሰማይ ሠራዊት፣ በምድርም ላይ በሚኖሩ መካከል የፈቀደውን ነገር እንዴት እንደሚያደርግ ፎርሙላ ያቀርባል፡፡

ወገኖች ሆይ፣ የእግዚአብሔር ፎርሙላ እንዲህ ይነበባል፡፡ ድሀ (ዝቅ) ያደርጋል፣ ባለጠጋም (ከፍ) ያደርጋል – ያዋርዳል (ዝቅ)፥ ደግሞም (ከፍ ከፍ) ያደርጋል!

ጆሮ ያለው ይስማ!  ሁሉን ቻይ እግዚአብሔር፣ እርሱ እንደወደደ በሰማይ ሠራዊት፣ በምድርም ላይ በሚኖሩ የሰው ልጆች መካከል ዝቅ፣ ከፍ – ዝቅ፣ ከፍ፣ ከፍ ያደርጋል
እደግመዋለሁ፣ ጆሮ ያለው ይስማ! የእግዚአብሔር ፎርሙላ እንዲህ ይነበባል – እግዚአብሔር ዝቅ፣ ከፍ – ዝቅ፣ ከፍ፣ ከፍ ያደርጋል

ወገኖች ሆይ፣ በሕይወታችን ጉዞ መውረድና መውጣት መውደቅ፣ መነሳትና መክበር ሁልጊዜም ይኖራል! ማልቀስና መሳቅ ማዘን፣ መጽናናትና መደሰት  ሁልጊዜም ይኖራል! ማጣትና ማግኘት መዝራት፣ ማጨድና መብላት ዘወትር ይኖራል! ውርደትና ክብር ስደት፣ እረፍትና መንገሥ ዘወትር ይኖራል!

ታውቃላችሁ፣ መደኽየት፣ መበልጸግ መበተን፣ መልቀምና ማባዛት ዘወትር ይኖራል፡፡ ስለሆነም፣ አግኝተን ስናጣ፣ አጥተንም ስናገኝ የእግዚአብሔርን ፎርሙላ በጭራሽ አንርሳ! ያገኘም – ያጣና፣ ያጣም – ያገኝና፣ የሆነች ቦታ ላይ – መገናኘት አለና፣ የእግዚአብሔርን ፎርሙላ ማስታወስ ይገባል!

ወገኖች ሆይ፣ የእግዚአብሔር ፎርሙላ እንዲህም ይቀርባል – እግዚአብሔር የኃያላንን ቀስት ሰብሮ ደካሞችን በኃይል ያስታጥቃል። የጥጋበኞችን መሶብ ደፍቶ የረሀብተኞችን ቡሀቃ ይሞላል! ብዙ የወለዱትን አድክሞ መካኖቹን በልጅ ይባርካል! የእግዚአብሔር ፎርሙላ –ይገድላል ያድናል፣ ሲኦል ያወርዳል፥ ያወጣል!

ስለዚህ፣ የቅድስት ሐና ቅኔ እንዲህ ይዘረፋል – እግዚአብሔር አዋቂ ነውና፥ አንታበይ፣ በኩራት አንናገር! እግዚአብሔርም ሥራን የሚመዝን ነውና፥ ከአፋችን የኵራት ነገር አይውጣ! እግዚአብሔር ዝቅ፣ ከፍ – ዝቅ፣ ከፍ፣ ከፍ ያደርጋልና
-----
ትምህርቱ ጠቅምዎታል? እንግዲያውስ ላይክ ያድርጉ፡፡ ጌታ ይባርክዎ!

--------------------------------

‹‹የወንጌላዊ እጮኛ›› አዲስ መጽሐፍ፣ በገበያ ላይ ውሏል፡፡ ለተጨማሪ መረጃ በ0911 678158 ወይም 0911 813092 ይደውሉ፡፡

No comments:

Post a Comment